ባጃጅ ውስጥ ተረስቶ ያገኘውን 150ሺህ ብር ለባለቤቱ የመለሰው የባጃጅ አሽከርካሪ አድናቆት እየተቸረው ነው

11921

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2015 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ በሚያሽከረከረው ባጃጅ ውስጥ ተሳፋሪ ረስቶት ያገኘውን 150ሺህ ብር ለባለቤቱ የመለሰው አሽከርካሪ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።

መኮንን ግርማ ኑሮውን ለማሸነፍ እና የነገውን ተሰፋ ብሩህ ለማድረግ በባጃጅ አሽከርካሪነት ተቀጥሮ የሚሰራ ወጣት ነው።

ወጣቱ መጋቢት 15 ቀን 2015ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ የተለመደ ስራውን እያከናወነ ሳለ የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ኡስማን ከሳቢያን ኦርቢት ተብሎ ወደሚጠራው የከተማው ክፍል ለመጓዝ መሳፈራቸውን ተናግሯል።

ይህ ከሆነ ከአንድ ሰዓት በኋላ “ስልክ ተደውሎ ባጃጁ ላይ ገንዘብ ወድቆ እንደሆነ እንድመለከት” ተነገረኝ ይላል ወጣቱ አሽከርካሪ መኮንን።

በተነገረው መሰረት ወደ ተሳፋሪ ወንበር ላይ ዞሮ ሲመለከት በላስቲክ የተጠቀለለ 150ሺህ ብር በማግኘቱ ወዲያው ወደ ድሬዳዋ ፖሊስ ትራፊክ ዳይሬክቶሬት በማምራት ብሩን ለባለቤቱ መመለሱን ገልጿል።

ገንዘቡን ለባለቤቱ መመለሱ እንዳስደሰተው የተናገረው ወጣቱ፤ የራስ ያልሆነ ገንዘብ ለግል መጠቀም የህሊና ቁስል በመሆኑ በራስ ወዝ ብቻ ሀብት ማፍራት እንደሚገባ መናገሩን ከድሬዳዋ ፖሊስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ገንዘባቸው የተመለሰላቸው አቶ መሐመድ ኡስማን በበኩላቸው ገንዘባቸው በጠፋ በአንድ ሰዓት ውስጥ የተሳፈሩበትን የባጃጅ የጎን ቁጥር ለትራፊክ ፖሊስ በመናገር በፍጥነት ገንዘባቸው በመገኘቱ መደሠታቸውን ገልጸዋል።

አቶ መሐመድ ለድሬዳዋ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት እና ለወጣት መኮንን ግርማ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ስነ-ምግባር ያለው አሽከርካሪ እንዲፈጠር እየሰራን ያለው ስራ ፍሬ እያፈራ መምጣቱን ይህ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም