ብሩህ ነገን የሰነቁ እንስቶች

543

የሰው ልጆች ከፍጥረት እስከ ዕለተ ሞት ባሉት የሕይወት ዑደቶች ውስጥ በሚገጥሟቸው መልከ ብዙ ፈተናዎች ሳቢያ ራሳቸውን ለቀቢጸ ተስፋ ይዳርጋሉ፤ ተገደውም ወደ ማይፈልጉት ሕይወት ይገባሉ።

በተለይም ሴቶች በሚገጥሟቸው አይነተ ብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጫናዎች ሳቢያ በበርካታ የህይወት ውጣ ውረድ ወስጥ ያልፋሉ፤ በሂደቱም ለአካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ በርካቶች ናቸው፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ቃልኪዳን በላይነህ (በግል ፍላጎቷ ስሟ የተቀየረ) በወጣትነቷ ትዳር መስርታ፣ልጆችን ወልዳ ለመሳም በቅታለች፡፡

ዳሩ ግን ባለቤቷ በድንገተኛ አደጋ በመሞቱ ምክንያት ህጻን ልጆቿን ይዛ ለአስከፊ የኢኮኖሚ ችግር መዳረጓን ትናገራለች።

በዚህም ራሷንና ልጆቿን ህይወት ለማቆየት ወደ ማትፈልገው የወሲብ ንግድ ሕይወት ውስጥ ለመግባት መገደዷን ነው የገለጸችው፡፡

በህፃንነት ዕድሜ ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረገችው ሳምራዊት (በግል ፍላጎቷ ስሟ የተቀየረ) በበኩሏ በአካል ጉዳተኝነቷ ምክንያት ተንቀሳቀሳ መስራት ባለመቻሏ ከተወለደችበት ገጠራማ ስፍራ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን ትናገራለች፡፡

በአዲስ አበባም ህይወቷን በልመና ስትመራ ቆይታለች፡፡

ሌላኛዋ ባለታሪካችን ሔዋን (በግል ፍላጎቷ ስሟ የተቀየረ) ወደ ማትፈልገው ህይወት ውስጥ ስትገባ የሚያጋጥማት ማህበራዊ ፣ አካላዊ ጥቃት እና ስነልቦናዊ ጫና ቀላል አይደለም ትላለች።

እሷም ኑሮን ለማሸነፍ የገባችበት የህይወት መስመር ወደ አላስፈላጊ ሱስ ውስጥ እንድትገባና ለስነ ልቦናዊ ቀውስ እንድትጋለጥ እንዳደረጋት ገልጻለች።

መንግስት በመሰል ችግር ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከዚህም ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ለመታደግ የሚያስችልና “ለነገዋ” የተሰኘ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል አንዱ ነው፡፡

ማዕከሉ ለተለያዩ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ  ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን  በስነ ልቦና የምክር አገልግሎት እና በተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎች በመስጠት ብሩህ ነገን ለማቀዳጀት ስራ ጀምሯል።

እነ ቃልኪዳን፣ ሳምራዊት፣ ሔዋንና ሌሎች በችግር ውስጥ የነበሩ ሴቶችም ‘የነገዋ’ የተሰኘውን የተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን ተቀላቅለው የተሻለ ነገን ለመኖር ተስፋ ሰንቀዋል፡፡

በማዕከሉ በሚሰጣቸው ሙያዊ ስልጠናና የምክር አገልግሎትም ወደ ተረጋጋ መንፈስ እንዲመለሱ፣ የሕይወት ተሞክሮ እንዲቀስሙ፣ ነጋቸውን ለማሳመር እንዲነሳሱ ስለማድረጉም ይናገራሉ።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ መከፈቱ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ትልቅ ብስራት መሆኑን ገልጸው፤ መሰል ማዕከላትም በአገር አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

“የነገዋ” የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሄርጳሳ ጫላ ማዕከሉ ወደ ስራ ከገባ አንድ ወር በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ 500 ሴቶችን ተቀብሎ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሰልጣኞች ከማዕከሉ ሲወጡ ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲችሉ የሚያደርግ በልዩ የክህሎት፣ የስነ ልቦና  እና የሙያ  በአጠቃላይ በ18 አይነት  የስልጠና ዘርፎች እያሰለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ስፌት፣ ስነ ውበት፣ የምግብ ዝግጅት፣ የከተማ ግብርና፣ የሕጻናት እንክብካቤና ሌሎች ዘርፎች  ከሶስት ወር እስከ ስድስት ወር እንደሚያሰለጥን ነው የገለጹት።

ከስልጠናው በኋላ ለሰልጣኞች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ማዕከሉ በትብበር እየሰራ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማእከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ከፍት መሆኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም