የኢትዮጵያን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ  ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-- የፌደራል  ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን 

152

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ  ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የፌደራል  ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲያደርግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን አማካሪና የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በሎጅስቲክስ፣ በትራንስፖርት፣ በታዳሽ ኃይል እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።

በአንጻሩ እንደ ሀገር ትኩረት የሚፈልጉ የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያ የሚጠይቁ የመንግስትን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን አመላክተዋል።

ለአብነትም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና የማበረታቻ ስርዓት ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ያሉ የቴክኖሎጂ አሰራሮች እና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ በርኦ ሀሰን ዲጂታላይዜሽን ለዘርፉ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ወሳኝ መሆኑን  ጠቅሰው፥ እስካሁን በተተገበሩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ለሱፐርቪዥን ቡድኑ ገልጸዋል።


 

ዘርፉን ለማሳደግ ሁሉም አይነት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ናቸው።

በዚህም የሎጂስቲክ ዘርፉን አፈጻጸም ማሳደግ መቻሉን እና ከዚህ የበለጠ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም