በደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በተያዘው ዓመት ከ713 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ

155

ቦንጋና ዲላ፤ሚያዚያ 18/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ713 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደተግባር መገባቱ ተገለጸ።

የየክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች ከደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮዎች ጋር በመተባበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ መሆኑም ተመላክቷል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ከበልግ ወቅት ጀምሮ ከ372 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ ይካሄዳል። 


 

አስካሁንም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በመቀናጀት ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸው የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ መርሀግብር ተከላ መጀመሩን አስረድተዋል። 

"ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 32 ሚሊዮን ቡና እንዲሁም 27 ነጥብ 9 ሚሊዮኑ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሃይለማርያም፣ ችግኞቹን በተያዘው የበልግ ወቅት ተክሎ ለማጠናቀቅ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ቀሪዎቹን ችግኞች በክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በክልሉ በየዓመቱ የሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የውሃ አቅምን በመጨመርና የመሬት ለምነትን በማጎልበት ለግብርና ልማቱ ውጤታማነት አስተዋጾ ማድረጋቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።   

ህብረተሰቡም በችግኝ ተከላ ሲያደርገው የነበረውን ተሳትፎ በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት፣ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ በክልሉ ለአርንጓዴ ልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። 


 

በተያዘው ዓመትም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ341 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከእዚህ ውስጥ ከ149 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በተያዘው የበልግ ወቅት እንደሚተከሉ ጠቁመው፣ ቀሪ 192 ሚሊዮን ችግኞች በክረምት ወራት ይተከላሉ ብለዋል።

ችግኞቹ ከክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮ ጋር በመተባበር መዘጋጀታቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራው በተቀናጀ መንገድ ይከናወናል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተተከሉ ችግኞች የክልሉን የደን ሽፋን እያሳደጉት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አቶ ውብሸት እንዳሉት የአረንጓዴ ልማት ሥራው የደን ሽፋኑን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን በእጅጉ እያገዘ ነው።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ተገቢውን ጥበቃና ክብካቤ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ባለው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ከ288 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የጽድቀት መጠናቸውም 86 በመቶ መሆኑን የቢሮው መረጃ ያሳያል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም