ቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ ስራ መጀመሩ ስታርትአፖችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የተያዘው ቁርጠኝነት ያግዛል

146

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ ስራ መጀመሩ ስታርት አፕንና የስራ ፈጠራ እንዲጎለብት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ተናገሩ።

በአፍሪካ የስራ ፈጠራና ስታርትአፕን የሚደግፈው ቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ በትላንትናው እለት ስራውን በይፋ ጀምሯል።

ኢኒሼቲቩ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አነሳሽነት በአፍሪካ በተለይ ኢንቨስትመንትን፣ ስራ ፈጠራንና ስታርት አፕን ለመደገፍ የሚሰራ ነው።

በኢንሼቲቩ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ በሀገራችን መጀመሩ የስራ ፈጠራና ስታርትአፕን እንዲጎለብት ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢንሼቲቩ በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳርን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቀጣይም  የዜጎችን የፈጠራ አቅም ለማጎልበት እና ዲጂታልን የመጠቀም ባህል ለማጎልበት ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀል።

የስራ ፈጠራና ስታርት አፕን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አላማ ይዞ እየሰራ የሚገኘውን የቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭን ከግብ ለማድረስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የጀመራቸውን የጋራ ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ አክለዋል።



የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ በበኩላቸው ኢኒሸቲቩ ስታርትአፖች በጋራ ሆነው በዘርፉ ላይ በመስራት ለውጥ እንዲያመጡ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። 

መንግስት በሀገሪቱ ስራ ፈጠራን ለማበረታታት ብሎም የቲምቡክቱ ኢንሼቲቭን ወደ ተግባር ለመቀየር ፖሊሲዎችን ከማዘጋጀት ጨምር ሌሎች በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘመንን ለመገንባት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢንሺቲቩ አፍሪካውያን በጋራ እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም