ለትንሣኤ በዓል ጤናማ የገበያ ስርጭትና ዋጋ እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ ነው - የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ

93

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- ለትንሣኤ በዓል የምርት አቅርቦትን በማሳደግ የዋጋ መረጋጋት እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ።

በኅብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ጫና ለመከላከል ግብረ ሃይል አደራጅቶ ስራ መጀመሩን ቢሮው ገልጿል።

ለትንሣኤ በዓል በዋናነት በጀሞ፣ በላፍቶ፣ በአቃቂ፣ በለሚ ኩራና በኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም በ188 የእሁድ ገበያዎች የዋጋ መረጋጋት እንደሚታይ ቢሮው ገልጿል።

በቢሮው የንግድና ግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ፍስሐ ጥበቡ ገበያው የተረጋጋ እንዲሆን ከነገ ጀምሮ በእሁድ ገበያዎች ምርቶች በስፋት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

በመዲናዋ የነበረው የዋጋ ንረት አሁን ላይ እየተረጋጋ መምጣቱንም ነው ምክትል ቢሮ ሀላፊው የጠቀሱት፡፡

በመንግሥት የገበያ ማዕከላትና በእሁድ ገበያዎች እየተሸጡ ያሉ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዲኖራቸው መደረጉ ለገበያ መረጋጋት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አብራርተዋል።

በለሚ ኩራ፣ በኮልፌ እና በአቃቂ ቃሊቲ ዘመናዊ የመንግሥት የገበያ ማዕከላትም ከሰኞ ጀምሮ ከ154 በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚሳተፉበት የባዛርና የንግድ ትርዒት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በመንግሥት የገበያ ማዕከላትና የእሁድ ገበያዎች ከ76 በላይ አርሶ አደሮችና ከአንድ መቶ በላይ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንደሚያቀርቡ ጨምረው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የከተማ ግብርናና አርሶ አደር ኮሚሽንም የግብርና ውጤቶቹን ለኅብረተሰቡ እንደሚያቀርብ እንዲሁ።

የቁም እንስሳት በሚሸጡባቸው በአቃቂ፣ በየካ ካራአሎ፣ ሸጎሌ፣ በአዲስ ከተማ ብርጭቆ ፋብሪካ አካባቢዎች ጤናማ የገበያ ሥርጭትና ግብይት እንዲኖር በቂ ዝግጅት መደረጉን አቶ ፍስሐ አመላክተዋል።

ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች በግብይት ውስጥ እንዳይገቡና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ጥብቅ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ሊስተዋሉ የሚችሉ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም