ኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

77

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ እና የኮንጎ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት፣ ሲቪል አቪየሽንና መርቻንት ኔቪ ሚኒስትር ኦነሬ ሳይ ተፈራርመዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፤ ስምምነቱ ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነው ብለዋል።


 

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ሁለቱን ሀገራት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በማስተሳሰር በኩልም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

ስምምነቱ በበረራ ምልልስ፣ በመዳረሻ ቦታ፣ በትራፊክ መብቶች፣ በአውሮፕላን ዓይነት፣ በተወካይ አየር መንገዶች ቁጥር እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ገደብ የማያስቀምጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ጊዜ ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ በሳምንት ሰባት በረራ የሚያደርግ ሲሆን ስምምነቱ ወደ ብራዛቪልና ፖይንትኖይር ከተሞች የሚያደርገውን በረራ በማጠናከር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ምቹ ሂደት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኮንጎ ሪፐብሊክ የሚገኙ የአየር መንገዶች እንዲጠናከሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቁመዋል።

ይህም የአፍሪካ አየር መንገዶች በአፍሪካ አየር ገበያ ያላቸውን ድርሻ ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

ስምምነቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡

የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነትና ትስስር አስፈላጊነትን በመገንዘብ ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት በሁሉም አህጉራት ከሚገኙ 112 ሀገሮች ጋር የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን መፈራረሟንም ጠቁመዋል።

የኮንጎ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት፣ ሲቪል አቪየሽንና መርቻንት ኔቪ ሚኒስትር ኦነሬ ሳይ በበኩላቸው ሀገራቸው ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።


 

ስምምነቱ የሁለቱ አገራት መሪዎች በተስማመሙት መሰረት መከናወኑን ጠቁመው ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢቪየሽን ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋግር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

ኢትዮጵያና የኮንጎ ሪፐብሊክ የረዥም ጊዜ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም