በዘንድሮው ዓመት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል

153

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- በዘንድሮው ዓመት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ ገለፀ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ የችግኞችን የጽድቀት መጠንና የዘንድሮ ዓመት ዝግጅቶችን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን አዳኣ ወረዳ ጉብኝት አድርጓል።

ከጉብኝቱ ቀጥሎ በቢሾፍቱ ከተማ የ2016/17 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅትና የቀጣይ የስራ አቅጣጫን አስመልክቶ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፤ ጉብኝቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን በመገምገም የቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

በ2015/16 ዓ.ም በጀት አመት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን የደንና የፍራፍሬ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

በሁለት ዙር በተካሄደ የዳሰሳ ጥናትም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን 90 ከመቶ ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

ለዚህም በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳኣ ወረዳ በተደረገው የመስክ ምልከታ በተሰራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የችግኝ ተከላ ስራ ተራቁቶ የቆየን አካባቢ በደን መሸፈን መቻሉም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ በለሙ የተፋሰስ ይዞታዎች ላይ በእንስሳት ማድለብና በንብ ማነብ መስኮች የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በ2016/17 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዕቅድ ከተያዘው የ6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ ከዕቅድ በላይ 7 ነጥብ 3 መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሚተከሉ ችግኞችም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለተከላ ቦታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እና የውሃና ኢነርርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማድረግ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩም በግብርና ምርታማነት በማሳደግ ለዜጎች በስራ ዕድል ፈጠራና በሥነ-ምግብ ስርዓት መሻሻል አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቀጣይነት ያለው የውሃ ፍሰት በመፍጠር ለመስኖ ምርታማነት፣ ለግድቦች የውሃ ደህንነት እና ለንጹህ የምንጭ ውሃ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኤሊያስ ከድር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

በዘንድሮው መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በመጪው ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዜጎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃና ለግብርና ምርታማነት አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸውም በዚሁ ወቅት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም