በፓሪስ ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ለመሳተፍ የሚረዳ ዝግጅት እየተከናወነ ነው

113

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብስክሌት ተወዳዳሪዎች በፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ  ለማግኘት በመቀሌ ልምምድ እየሰሩ መሆኑን  የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽኑ ገለፀ።

የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም ወልደአብ እንደገለፁት ከተለያዩ ክለቦች የተወጣጡ ስድስት ወንድና አምስት ሴት ብስክሌተኞች የኦሎምፒክ ተሳትፎ ለማግኘት በመቀሌ ልምምድ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ክለቦች ያሉ ኢትዮጵያውያን ብስክሌት ተወዳዳሪዎችም፤ በተለያየ ውድድሮች በመሳተፍ በድምር ውጤት ለኦሊምፒክ የሚያሳትፋቸውን ነጥብ ለማግኘት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ለፓሪስ ኦሊምፒክ ለማለፍ ቀደም ብሎ ዝግጅት መጀመሩና ብስክሌተኞች የውድድር መድረክ ማግኘታቸው  መልካም የሚባል ጅምር መሆኑን ተናግረዋል።

የብስክሌት ብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ንጉሤ ገብረዮሐንስ በበኩሉ በጋና አክራ ከተሳተፉበት የመላው አፍሪካ ጨዋታ ውድድር በተሻለ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል ።

አሁን ላይ የትግራይ ክልል በሚያዘጋጀው ዓመታዊ ብስክሌት ውድድር ለመሳተፍ በአክሱም ከተማ 11 ብስክሌተኞች እንደሚገኙ ገልጿል።

እነዚህ ብስክሌተኞች በጋና አክራ በተከናወነው የመላ የአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፈው የነበሩ መሆናቸውንና በውድድሩ ክለቦቻቸውን ወክለው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 በተከናወነው በሪዮ ኦሊምፒክና፤ በ2021 በተደረገው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በበስክሌት ስፖርት መሳተፏ የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ መድረክም ዘንድሮ በጋና አክራ በተከናወነው የመላው አፍሪካ ጨዋታ፤ በስድስት ወንዶችና በአምስት ሴቶች በመሳተፍ፤ በአንድ የብር ሜዳሊያ ከአፍሪካ ሰባተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም