በተቋማት የሚታዩ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በሚዲያ ተቋማቱ ቅርንጫፎች የተጀመሩ የይዘት ሥራዎች መጠናከር አለባቸው

159

አዳማ፤ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፡- በተቋማት የሚታዩ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር  ችግሮች እንዲፈቱ በሚዲያ ተቋማቱ ቅርንጫፎች የተጀመሩ የይዘት ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የአመራር አባላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዳማ ቅርንጫፍና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዳማ ማሰራጫ ጣቢያን ጎብኝተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በዚህ ወቅት እንደገለፁት አዳማ ከአዲስ አበባ ቀጥላ ሁለተኛዋ የቱሪዝምና ኮንፈረንስ ከተማ መሆኗን ጠቅሰዋል።

በሚዲያ ተቋማቱ ቅርንጫፎች እየተከናወኑ ያሉት ኩነቶችና የፕሮጀክት ስራዎች የዋናው መስሪያ ቤትን ጫና ከመቀነሳቸው በተጓዳኝ ለህብረተሰቡም የቀረቡ ናቸው ብለዋል።

በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት በምልከታና በዳሰሳ ጥናት የሚያገኙትን ግኝቶች ከኩነት ባለፈ የፕሮጀክት ስራዎችን በመስራት ረገድ የቅርንጫፎቹ ሙያተኞች እያከናወኑ ያሉትን አበረታች ተግባር አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የዞኖችና የከተማ አስተዳደሮችን ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግሮችን ከመፍታት  አንጻር እየተሰሩ ያሉ የይዘት ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

ቅርንጫፎቹ ከዋናው መስሪያ ቤት ጋር በቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ያላቸው ትስስር፣ የዜና ቅብብሎሽና ቅንጅታዊ ስራ ይበልጥ መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባልና የሚዲያ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አቡኔ ዓለም በበኩላቸው የኢዜአ አዳማ ቅርንጫፍ ከቢሮ አደረጃጀት ጀምሮ ጥሩ ይዘት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቅርንጫፉ ከዕለታዊ ኩነቶች ባለፈ በከተማዋ በሚካሄዱ ሀገራዊና ክልላዊ መድረኮች የሀገሪቷን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች፣ ውስንነቶችና የቀጣይ ትኩረትን መሰረት ያደረጉ የፕሮጀክትና የዕቅድ ሥራዎች ማከናወኑን በጥሩ ጎን ተመልክተናል ብለዋል።

በተለይም በአዳማ የሚካሄዱ ሀገራዊና ክልላዊ ሥራዎች ቅርንጫፉ የሚሸፍናቸውና ከዋናው መስሪያ ቤት የጊዜ፣ የትራንስፖርትና የወጪ ጫናዎችን የቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅርንጫፉ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ሚዲያዎች ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር አለበት ያሉት ወይዘሮ አቡኔ፤ በዙሪያው ባሉ አካባቢዎችም ተንቀሳቅሶ ሽፋን መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የአመራር አካላቱ በተመሳሳይ የኢቲቪ የአዳማ ቅርንጫፍ የማሰራጫ ጣቢያን የተመለከቱ ሲሆን ጣቢያው ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም