የኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመምከር በስምምነት ተጠናቀቀ

107

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2016(ኢዜአ)፦ ለሁለት ቀናት በጅቡቲ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመምከር በስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የጁቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት አገራቱን በውኃ፣ በፈጣን መንገድ፣ ሃይል አቅርቦት፣ ወደብ አገልገሎት እንዲሁም አጠቃላይ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ማስተሳሰር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር መምክራቸው ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን፤ የአገራቱ ወዳጅነት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም የአገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት በበርካታ መስኮች ለማጠናከር በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የአገራቱን ግንኙነት በማሳለጥ ረገድ የኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ሚናው ከፍተኛ ሲሆን፤ የጋራ ኮሚሽኑ በጅቡቲ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ አጠናቋል፡፡

ስብሰባውን የኢፌዴሪ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ እና የጅቡቲ የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ሀሰን ሁመድ ኢብራሂም በጋራ መርተውታል፡፡

በስብሰባው በ16ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች፣ በስምምነቱ ወቅት በሁለቱም ወገን ክትትል ተደርጎባቸው መፍትሄ እንዲሰጥባቸው አቀጣጫ የተሰጠባቸው ጉዳዮችን የአፈጻጸም ሂደት ተገምግሟል፡፡

በሁለቱ አገራት ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፎች፣ በኢንቨስትመንትና በህገ-ወጥ የጠረፍ ንግድ፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ዘርፎች በተለይም በዲኪል-ጋላፊ መንገድ ግንባታ አፈፀፃም ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

 የመንገድ ፈንድ ክፍያ፣ የወደብና ትራንዚት እንዲሁም በጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎች ለመፍታት እየተደረጉ ባሉት ጥረቶች ላይ ምክክር መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

በዚሁ መነሻነት አገራቱ ከዚህ ቀድም የተፈራረሙት የወደብ እና ትራንዚት አገልግሎቶች፣ የጉምሩክ ፕሮቶኮል ስምምነት እና የመልቲሞዳል ስምምነቶች ለማሻሻል የቴክኒክ ኮሚቴዎች መዋቀሩ ተገልጿል።

በመጪው ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጅቡቲ በሚካሄደው 17ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ምክክር መድረክ የሚሆኑ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መድረኩ በስምምነት ተጠናቋል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ለረዥም ጊዜ የቆየ የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በስብሰባው የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት አገራቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በተለይም በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን የሎጅስቲክስ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የጅቡቲ የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ሀሰን ሁመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የኢትዮጵያንና የጁቡቲን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር መሰል መድረኮች ትልቅ አስተዋዕጾ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡


 

ስብሰባውም የጋራ መግባባት የሰፈነበት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በጅቡቲ በተካሄደው የኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ  የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር  አለሙ ስሜን ጨምሮ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል፡፡

በጅቡቲ ወገን ደግሞ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የመሠረተ-ልማት ሚኒስትር ሀሰን ሁመድ ኢብራሂም፣ የግብርና ሚኒስትር መሀመድ አህመድ አወሌ እንዲሁም የአገሪቷ የጉምሩክ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም