ኮሚሽኑ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥን በራስ አቅም ለመሸፈን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል

105

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡ የፌደራል አደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽን የአደጋ ምላሽ አሰጣጥን በራስ አቅም ለመሸፈን እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ  የፌደራል ተቋማት የሱፐርቪዥን ቡድን ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተቋቋመው የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን  የአደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽንን የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡


 

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ የፕላንና የመንግስት ኢንቨስትመንት ዴስክ ኃላፊ እና የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተባባሪ ከተማ ቱፋ፤ ኮሚሸኑ በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የፖሊሲ፣ የአሰራርና የመመሪያ  ማሻሻያ ማድረጉን ተመልክተናል ብለዋል፡፡ 

አደጋን ለመቀነስ ጠንካራ የአደጋ ስጋት ልየታ፣ ክትትል እና ትንበያ በማድረግ እየሰጠ ያለው የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎትም የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉት 3 ሺህ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰራጫ ጣቢያዎች አማካኝነት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የተጠቃሚ ልየታን፣ ምዝገባን እና የእርዳታ ቁሳቁስ ስርጭትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እርዳታ ባቋረጡበት ወቅት የአደጋ ምላሽ አሰጣጥን በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመራቸውን ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ስራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ የእርዳታ እህል ማከማቻ መጋዘኖችን ደረጃ  ለማሻሻል እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አሰራሩን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የአደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሐይዳሩስ ሃሰን በበኩላቸው፤ አሁን ላይ በቂ የሚባል የመጠባበቂያ እህል ክምችት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ባደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ መሰረትም ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ የራስ አቅምን በመጠቀም ረገድ እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን  ገልጸው፤ ከሱፐርቪዥን ቡድኑ ለተሰጡ አስተያየቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም