ምክር ቤቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን እንዲያስተካክል አሳሰበ

136

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡-  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መሰረታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን እንዲያስተካክል አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የአገልግሎቱን የ2016 በጀት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ገምግሟል።


 

በዚሁ ጊዜ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተቋሙ የሲቪል ምዝገባ ቁጥጥርና ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት አንስተዋል።

ዜጎች በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያሰሙ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመስክ ምልከታ ጭምር ማረጋገጣቸውንም ነው የተናገሩት።

ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየታየበት ያለውን ውስብስብ ችግር ከመሰረቱ ሊፈታ እንደሚገባም ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያሳሰቡት።

ተቋሙ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ለተገልጋዩና ለአገልጋዩ ምቹ የሆነ የስራ ከባቢን ከመፍጠር አኳያ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑንም ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተናገሩት።

በድንበር አካባቢ ያለው የቁጥጥር ስርዓት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝወውር መበራከት ምክንያት መሆኑንና ለዚህ ደግሞ ተቋሙ የድንበር ቁጥጥር ስርዓቱን እንዲያጠናክር ነው ማሳሰቢያ የተሰጠው።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊትና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ተቋሙ በኢትዮጵያ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ ቢሆንም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ከሰው ሃይልና ከግብዓት ጋር ተያይዞ የተከማቹ ችግሮች አሉበት ።

አገልግሎቱ ካለበት የረጅም ጊዜ ውስብስብ ችግር አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ መስጠት አዳጋች እንደሆነ አንስተዋል።

የተቋሙን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የህግና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

እነዚህ ማሻሻያዎች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ያገኛሉ ብለዋል።

የድንበር አጠባበቅ ስርዓቱ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ያረጋገጡት ዋና ዳይሬክተሯ ተጨማሪ በጀትና የሰው ሃይል በመመደብ አስተማማኝ ስርዓት ለመዘርጋት ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጽገነት መንግስቱ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱ ከፓስፖርትና ከወሳኝ ኩነት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ የህዝብ ቅሬታ የሚነሳበት መሆኑን ተከትሎ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

ተቋሙ ከሚሰጠው አገልግሎት አስፈላጊነት አንጻር የሚፈለገውን ትኩረት አለማግኘቱን ጠቅሰው፣ ከህግ ማዕቀፍና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ መሟላት ላለባቸው ነገሮች ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በተቋሙ የሚያጋጥመውን ብልሹ አሰራር ማስቀረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የድንበር አጠባበቅ ስርዓቱን ጠንካራ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችንም መስራት እንደሚገባም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም