የታላቁ የሕዳሴ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

67

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- የታላቁ የሕዳሴ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ኢትዮጵያውያን በየተሰማሩበት መስክ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

'ዘመናዊነት ያለ ኤሌትሪክ አይታሰብም ' በሚል ርእስ የታተመና 358 ገጾች ያሉት ጥናታዊ መጽሐፍ  ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተበርክቷል።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ኢትዮጵያዊያን በገንዘብና በዕውቀታቸው ሰፊ ድጋፍ እያደረጉ ነው።

ከዚህ ውስጥም በገንዘብ 19 ቢሊዮን ብር፤ በአይነት ደግሞ ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ከሕዝብ ተሰብስቧል ነው ያሉት።

በዛሬው እለት ለጽሕፈት ቤቱ የተበረከተው መጽሐፍ በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በጎ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቁመዋል።

የመጽሐፉ አዘጋጅ ኢንጂነር አስቀናቸው ገብረየስ በበኩላቸው፤ በአሜሪካን አገር ለበርካታ አመታት በኤሌትሪክ ኃይል ዘርፍ ታላላቅ ስራዎችን በሚያከናውኑ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ያገኙትን ልምድ መነሻ በማድረግም በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ሲያዘጋጁት የቆዩትን መጽሐፍ 990 ቅጂ ለጽሕፈት ቤቱ ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

መጽሐፉ በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምርምር ለሚያደርጉ አካላት ዘመናዊ ዕውቀትን የሚያስጨብጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም