በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3/2013(ኢዜአ) ጤናማ ያልሆነ የአናኗር ዘይቤ በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ማድረጉ ተገለጸ።
ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር ሕመም፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካል ችግር፣ ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ የደም ስር ችግሮችና የመሳሰሉት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በእነዚህና መሰል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ በዓለም ላይ በየዓመቱ 41 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ደግሞ 15 ሚሊዮን የሚሆኑት ዕድሜያቸው በ30 እና 69 ዓመት መካከል የሚገኙ መሆኑን መረጃው ያሳያል።
በዓለም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከሚመዘገበው ሞት 85 በመቶ የሚሆነው እየተከሰተ ያለው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የስኳር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ እንደሚሉት ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መጨመር ምክንያት ነው።
ትንባሆና የአልኮል ውጤቶችን አብዝቶ መጠቀም፣ የሰውነት ክብደት መጠን መጨመርና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚመዘገበው የሟቾች ቁጥር በስኳር፣ ደም ግፊትና መሰል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ43 ነጥብ 3 በመቶ በላይ ሆኗል።
በተለይ የስኳር ህመምን በወቅቱ አለመታከም ለሌሎች በሽታዎች የሚያጋልጥ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሲሳይ፣ በተደረጉ ጥናቶች ጤናማ ያልሆነ የስኳር መጠን በአዋቂዎች ብቻ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
"የስኳር ሕመምን ለመከላከል ቀድሞ በመመርመር ማወቅ ይገባል" ያሉት ዶክተር ሲሳይ፣ በአገሪቱ 60 በመቶ የስኳር ታማሚዎች በወቅቱ ወደ ህክምና የማይመጡ መሆኑንም አመላክተዋል።
የስኳር ህመም ፈጥኖ ካልታከመ ለዓይነ ስውርነት፣ ለኩላሊት፣ ለነርቭና ለሌሎች ሕመሞች ሊያጋልጥ እንደሚችልም ነው ያመለከቱት።
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል የገለጹት የጤና ባለሙያው፣ ለበሽታዎቹ አጋላጭ ከሆኑ ዋና ዋና መንስኤዎች መጠንቀቅ እንደሚገባም መክረዋል።
የትምባሆ እና የአልኮል ውጤቶችን አለመጠቀም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር፣ እንደ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ ምግቦችን መመገብ በማዘውተር ጤናማ መሆን ይቻላል ብለዋል።
ቅባት፣ ጮማ፣ ጨው እና ስኳር የበዛባቸውን ምግቦች በመቀነስ እንዲሁም ጫት እና ሌሎች አጋላጭ የሆኑት ነገሮችን አለመጠቀም ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል እንደሚረዳም ነው የገለፁት።
በቋሚነት የጤና ምርመራ በማድረግ የጤና ሁኔታ ማወቅ በሽታዎቹን አስቀድሞ ለመከላከልና ህክምናን ለማቅለል እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።