የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ በባህርዳር አቀባበል እንደሚደረግለት ተገለጸ

ባህርዳር መስከረም 3/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ /አዴሃን/ አባላት ነገ በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ አስተባባሪ ኮሚቴው ገለጸ፡፡ የንቅናቄው የወጭ ፋይናንስ ኃላፊና የአቀባበሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይግዛው አጥናፉ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት የንቅናቄው አባላት ከኤርትራ ባህርዳር ከተማ ገብተዋል፡፡ ህዝቡ ለአባላቱ አቀባበል ለማድረግ በመፈለጉ ነገ ከአራት ሰዓት ጀምሮ በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም የአቀባበል ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። ላለፉት ስምንት ዓመታት በኤርትራ በረሃ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ  የቆዩት የአዴሃን አባላት በተዘጋጀው የአቀባበል ፕሮግራም ላይ ከህዝቡ ጋር እንዲተዋወቁ ይደረጋል። በአቀባበል ፕሮግራም የአዲሃን ሊቀመንበር ለህዝቡ ንግግር በማድረግ የድርጅቱን አላማ እንደሚያስተዋውቁም ኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል። ከባህርዳር ከተማና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ በተጨማሪም የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎች በአቀባበሉ ፕሮግራሙ እንደሚገኙ ይጠበቃል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም