ጁንታው የህወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት እየተደመሰሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጁንታው የህወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት እየተደመሰሰ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሠራዊት ጁንታውን የህወሓት ቡድን በመደምሰስ የሀፍረት ካባ እያከናነበው ነው ሲሉ የደቡብ ዕዝ የሰው ሀብት ልማትና የራያ ግንባር ሚዲያ አስተባባሪ ገለፁ።
አስተባባሪው ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ አጥፊው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሠራዊቱን ክብር ዝቅ በማድረግ ጀግና እሱ ብቻ እንደሆነ ሲሰብክ መቆየቱን ተናግረዋል።
ቡድኑ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ከሀሰት ትርክቱ ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝብ በንቀት ሲመለከት ነበር ብለዋል።
አሁን ራሱ በለኮሰው እሳት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በሁሉም አቅጣጫዎች ድባቅ እየመታ መፈናፈኛ አሳጥቶታል ሲሉም አክለዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት "ከእኔ በላይ ተኳሽ" እያለ ሲመጻደቅ የነበረውን የህወሃት ቡድን በመደምሰስ የሀፍረት ካባ አከናንቦታል ሲሉም ነው የገለፁት።
ይህም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሲቆሙ ምንም ሃይል እንደማያንበረክካቸው ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው፣ ለሰንደቅ ዓላማቸውና ለክብራቸው መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጀግኖች መሆናቸውን አሳይተዋል ነው ያሉት ኮሎኔል ደጀኔ።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕግ በማስከበር ተልዕኮው የአርሶአደር ማሳም ሆነ ንብረት አላበላሸም ያሉት ኮሎኔሉ ይህም ፀቡ ከቡድኑ እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ የሠራዊቱ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ መቀሌ ሲጠጋ የከተማ ውጊያ ልዩ ባህሪይ ያለው በመሆኑ ኅብረተሰቡ ቡድኑን 'ውጣልኝ' ማለት አለበት ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ዘራፊውን ቡድን ለሕግ እስከሚያቀርብ ድረስ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።