ኤጀንሲውና ኮሚሽኑ ያደረጉት ስምምነት ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

መስከረም 17/ 2014(ኢዜአ) ኤጀንሲውና ኮሚሽኑ ያደረጉት ስምምነት ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።
የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ስምምነት ተፈራርመዋል።

የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን እና ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አቶ ተስፋዬ ጎበዜ ስምምነቱን ተፈራርመዋል ።

አቶ ንጉሱ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ ሁለቱ ተቋማት ያደረጉት ስምምነት ስደተኞችንና ከስደት ተመላሾችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ኮሚሽኑ የአገራችን የስራ ገበያ የሚመች እንዲሆን ከተለያዩ መንግሰታዊ እና መንግሰታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የስራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በስራ ገበያ ውስጥ በቂ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግም ያስችላል ብለዋል።

ስምምነቱ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች በስራ ገበያው አምራች የሚሆኑበትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑንም ገልጸዋል።

ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን  ጎበዜ በበኩላቸው በተለያዩ አከባቢዎች በተናጥል ለስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች የስራ ዕድል ሲፈጠር መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን የተደረገው ስምምት ይህንኑ አስፍቶ ለመቀጠል የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ስምምነቱ በብሔራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ መሰረት በመንግስት ግዴታዎች እና በብሔራዊ ልማት ዕይታ ውስጥ የእያንዳንዳቸውን ግዴታዎች እና ተግባሮችን በማሟላት በተለይም ተመላሾችን፣ ስደተኞችን እና የሚኖሩበትን ማህበረሰብ በሥራ ገበያው ውስጥ በቂ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል።

የተሻሉ፣ ዘላቂ እና አመርቂ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የታቀዱ ልዩ ፕሮጄክቶችን ለማልማት፣ ለመተግበር እና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም