ቃልን በተግባር ያስመሰከረ አዲስ የፖለቲካ ባህል

በሚዲያ ሞኒተሪንግና ትንተና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባስተላለፉት መልእክት “ለዘመናት እየተከማቹ የመጡ ችግሮች በአንድ ፓርቲ መሪነትና መፍትሔ አመንጭነት ማስወገድ እንደማይቻል ታውቆ ተደራርበው የመጡብን ችግሮች ተባብረንና ተደምረን ለማሸነፍ መነሳት ይኖርብናል፤ በእኛ በኩል በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ሕልም ለስኬት እንዲበቃ እንሠራለን” ሲሉ አዲስ የፖለቲካ ባህል በሀገራችን እውን እንደሚሆን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው ይህ አዲስ የፖለቲካ ባህል በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት ዓብይ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል። እስካሁን ድረስም በአገሪቱ ለሚነሱ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መነሻና መድረሻ ሲሆን ተስተውሏል።

በኢትዮጵያ ሁሉን ያሳተፈ አዲስ የዴሞክራሲ ባህል እንደሚጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ ተደምጠዋል። በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ባዘጋጀው የምስጋና መርሃ ግብር ላይ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር  ዐብይ አህመድ ተገኝተው ነበር። በዚሁ ወቅት ባሰሙት ንግግግር በምርጫው  የኢትዮጵያ  ህዝብ እንዳሸነፈ  ስለሚቆጠር  ህዝብን  ወክለው  የተወዳደሩ   የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንደ ተወዳደሩበት  ክልልና አንደ አቅማቸው በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር።   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት አምስት ዓመታት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገለገሉትን ባሰናበቱበት ወቅት ባሰሙት ንግግር እሳቸው የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ይፋ በሚያደርገው የምርጫ ውጤት መሰረት አሸናፊ የሚሆን ከሆነ፣  የኢትጵያን ብልፀግና እውን ለማድረግ ኢትዮጵን ለማሻገር ከተዘጋጁ አካላት ጋር እጅና  ጓንት ሆኖ እንደሚሰራ ነበር የገለጹት።  “አሸናፊ ከሆንን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከፌደራል እስከ ክልል ባለው መንግስታዊ መዋቅር በአስፈፃሚ ቦታ እናሳትፋለን” በማለት አስረግጠው መናገራቸው ይታወሳል።

ቃል በተግባር እንዲሉ እነሆ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ ተጀምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ካቢኔያቸውን ይፋ ሲያደርጉ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በሃላፊነት ሾመዋል። ከኢዜማ ፓርቲ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር በመሆን ሲሾሙ ከኦነግ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም ከአብን አቶ በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ዓላማውም ዜጎች ባላቸው አቅምና ችሎታ ሁሉ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን እያገለገሉ የህብረተሰቡን እውነተኛ አኗኗር ተገንዝበው ችግሮች እንዲፈቱና ተቀራርቦ የመስራት ልምድ እንዲጎለብት ታሳቢ ያደረገ ነው።

ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን እንደገልጹት ሀገሪቷ ዘመናዊ አስተዳደር ከመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ መሪዎቿ የመንግስትና የህዝብ የኃላፊነት ቦታዎች የ “እኛ” ከሚሉት ወገን ውጭ እንዴ ዜጋ ችሎታና ብቃትን ታሳቢ አድርገው ወደ አመራርነት ማምጣት ፍጹም የማይታሰብ ጉዳይ ነበር። ይህ ደግሞ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ገጽታ የ “ተገለናል” መንፈስ እንዲላበስ አድርጎት ቆይቷል። አሁን ላይ ያለው ጅምር የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ነው የሚገልጹት።

ባለፉት 50 እና ከዛም በላይ ዓመታት በኢትዮጵያ የተነሱት የብሄር ንቅናቄዎች በአብዛኛው አካታች ባህል ከማጣት የሚመነጩ ነበሩ። ይህን ተከትሎ ለዓመታት ከማዕከላዊ መንግሥቱ ‘ተገፍተናል’ ወይም ‘አልተካተትንም’ የሚሉ ብሔሮች ያነሷቸው ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ማዕከላዊነትን እንዲይዝ አስችሎታል። በዚህም የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ከማቆጥቆጥና ከማደግ አልፎ አሁን ላይ ወደ ጎልማሳነት ተሸጋግሯል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታም ከብሔር ማንነት ጋር ተሳስረው አገራዊ ፖለቲካውን ከማጎልበት ይልቅ ማጦዝ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች አግላይ ፖለቲካን ለመታገል በሚል አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን ፈተና ላይ ሲጥሉ እንደቆዩ ለመረዳት ባለፉት 27 ዓመታት የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አካሄድ ማየቱ ብቻ በቂ ነው። በእነዚህ ዓመታት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመገለልም አልፎ እንዲሸማቀቁና ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ የሚያደርግ ገፊ እርምጃዎች ሲወሰድ ቆይቷል። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከመከፋፈልና እርስ በርስ ከማናቆር ባለፈ የፈየደው አንዳች ነገር የለም። በአንፃሩ ይህን ፖለቲካዊ አግላይነት ለመለወጥ ከብሔር ተኮር ፖለቲካዊ አዙሪት ወጥቶ ኅብረ-ብሔራዊ አደረጃጀት በመከተል አካታችነትን ገቢራዊ ማድረግ የደፈሩ ጥቂቶች ናቸው።

በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆኖ እናገኘዋለን።

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ፓርቲያቸው በምርጫው የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ መንግሥት መመስረት ከቻለ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን ባላቸው ዕውቀትና የስራ ልምድ በመንግሥታቸው መዋቅር እንዲካተቱ ይደረጋል ሲሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ከገዢው ፓርቲ ውጭ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ግለሰቦች በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የተሳትፎ ዕድል እንደሚሰጣቸው ደጋግመው መግለፃቸው የበዛው ህዝብ ይህን አዲስ ጅማሮ እውን ሲሆን ለማየት ለወራት በጉጉት ጠብቋል።

እንደተባለውም በምርጫው አብላጫ የመቀመጫ ወንበር በመያዝ መንግሥት የመሰረተው የብልጽግና ፓርቲና መሪው ቃልን በተግባር ማሳየት ችለዋል። በቅርቡ የተደረጉት የክልል መንግሥታት ምስረታዎች ላይም የታየው ይህንኑ ነው።

የተለያዩ ምሁራን በርካታ የዓለም ሀገራት ጥምር መንግሥት መስርተው እየተዳደሩ ስለመሆኑ እንደ እስራኤልና ጀርመንን ለማሳያነትን ያነሳሉ። አዳዲስና ከፓርቲው መዋቅር ውጭ የሆኑ ዜጎችን ባላቸው ብቃት በየደረጃው በኃላፊነት ቦታ እንዲቀመጡ ማድረግ ከአካታችነት በላይም ነው የሚሉም የበዙ ናቸው። ለዚህ እንደ መሞገቻ የሚያቀርቡትም የሃሳብ አብዝሃነትና የዜጎችን አገራቸውን የማገልገል መብትና ግዴታዎች እንዲሁም የገዥው ፓርቲና የተፎካካሪዎች የመደማመጥ ባህልን ከፍ የሚድረግ መሆኑን ነው።

በሌላ በኩል የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የሚረዳ ከመሆኑ ባለፈ ተቃዋሚዎች በርቀት ሆነው ትችት ሲያቀርቡበት የነበረውን አስተዳደር ተሳታፊ በመሆን ለችግሮች አማራጭ የሚሏቸውን ገንቢ ሃሳቦች እንዲያቀርቡ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም ታምኖበታል። አካታችነቱ ሥልጣን መጋራት ብቻም ሳይሆን ለጋራ ሀገር የሚደረግ ድምር መስዋእትነት በመሆኑ ሁሉም ወገኖች በቀናነት ተቀብለው ይበልጥ ሊያጎለብቱት ይገባል። ከፌዴራልና ከክልሎች ባለፈም እስከ ታችኛው የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር በማውረድ ገቢራዊ ቢደረግ የአካታችነት ባህሉ እንዲዳበር የሚያደርግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም