"ሰላማዊ ሰልፉ ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት መቆሙን በተግባር ያሳየበት ነው" ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለሚካኤል


ህዳር 4/2014(ኢዜአ)  "ሰላማዊ ሰልፉ ዳያስፖራው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት መቆሙን በተግባር ያሳየበት ነው" ሲል በቶሮንቶ ነዋሪ ሆነው ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለሚካኤል ገለጸ።

በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮጵያ ሕልውና መጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ ብሏል።

ምዕራባዊያን አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የሐሰት መረጃ ዘመቻ የሚቃወም ሰላማዊ ሠልፍ ትናንት በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ተካሄዷል።

በሰልፉ ላይ በካናዳ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተወካዮችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሟጋች የሆነው ጄፍ ፒርስና በሰላም ጉዳይ ላይ የሚሰራው ካናዳ ፒስ ኮንግረስ እየተባለው የሚጠራው ቡድን ተወካዮች በሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል።

'የኢትዮጵያዊያን ማኅበር በቶሮንቶና አካባቢው' አባል ጋዜጠኛ ብርሃኑ ተክለሚካኤል በሰላማዊ ሰልፉ ላይ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን አስመልክቶ እያሰራጩት ያለውን ሀሰተኛ መረጃ እንዲያቆሙ ጥሪ መቅረቡን ለኢዜአ ገልጿል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊትና ያደረሰውን ውድመትም የሚያወግዙ መልዕክቶች መተላለፋቸውን አመልክቷል።

"ምዕራባዊያን አገራት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ"፣ "ምዕራባዊያን አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው"፣ "ኢትዮጵያ የማንንም ጣልቃ ገብነትና ጫና አትቀበልም"፣ "ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤ አሁንም ሉዓላዊነቷ ተከብሮ ይቀጥላል" እና "ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያሰራጩ ያሉትን የሐሰት መረጃዎች ያቁሙ" ሰልፈኞቹ ይዘዋቸው ከወጡት መፈክሮች መካከል ይገኝበታል።

ሰላማዊ ሰልፉ በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የአገር ሕልውና ዘመቻውን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን መቆሙን በተግባር አሳይቷል ነው ያለው ጋዜጠኛ ብርሃኑ።

ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ልዩነቶቹን ወደ ጎን ትቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ በጋራ መቆሙንና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር እንደማይደራደርም በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ማሳየቱን አመልክቷል።

በካናዳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮችና የሃይማኖት አባቶች በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ንግግር አድርገዋል።

በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የማስጠበቅና የሐሰት መረጃዎችን የማክሸፍ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙና ይህም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጿል።

በካናዳ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በቀጣይ ሰላማዊ ሰልፎችን ጨምሮ የምዕራባዊያን አገራትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙና የአገር ሕልውና ዘመቻውን የሚደግፉ መርኃ ግብሮች እንደሚያዘጋጁም ጠቁሟል።

በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮጵያ ሕልውና መጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉም ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም