በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የበለጸገ "ቻት ቦት" የተባለ የባንክ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የበለጸገ "ቻት ቦት" የተባለ የባንክ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ይፋ ሆነ

መጋቢት 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የበለጸገ "ቻት ቦት" የተባለ የባንክ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ይፋ ሆነ።
ለኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ያበለጸገውን "ቻት ቦት" የተባለ የደንበኛ አገልግሎት መስጫ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና እና የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት ደርቤ አስፋው በተገኙበት በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የደንበኞች አገልግሎት መስጫ "ቻት ቦት" መተግበሪያ ወይም ድረ ገጽ ሳይሆን በቴሌግራም Coop KooBot ብሎ በመፈለግ ወይም በባንኩ ድረ ገጽ ላይ ተጭኖ በሚገኝ የቻት ቦት ምልክት ላይ በአማርኛ፣አፋን ኦሮሞና እንግሊዝኛ መረጃ የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤የደንበኞች አገልግሎት መስጫ "ቻት ቦት" ስለ ባንኩ መረጃ፣እገዛ በሚሹ ጉዳዮች፣ስለ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ቅሬታና ግብረ መልስ መረጃ ይሰጣል፡፡
የባንኩ ደንበኞች የትም ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን መረጃ በቻት ቦት 24 ሰዓት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ኢንስቲትዩቱ የፋይናንስ ተቋማት የዲጂታል ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ ለባንኩ የተዘጋጀው "ቻት ቦት" ያለምንም ክፍያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የደንበኛ አገልግሎት መስጫን ለማበልጸግ አንድ ዓመት እንደፈጀ ገልጸው፤ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ማድረግ ይገባል፤ እኛም ተከታታይ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራባቸው ዘርፎች ፋይናንስ ተቋማት ቢሆኑም አገልግሎቱን በማስፋት በግብርና፣ጤና እና ሌሎች ተቋማት ላይም ቴክኖሎጂዎችን እያበለጸገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ የፋይናንስ ስርዓትን በማዘመን፤የአገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍና የግልጽነት ስርዓትን በማስፈን እንዲሁም ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብን በመቆጠብ የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ፕሬዝዳንት ደርቤ አስፋው፤የደንበኞች አገልግሎት መስጫው ደንበኞች በርካታ መረጃዎችን ባሉበት ቦታ ሆነው ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎት መስጫው ከአማርኛ፣አፋን ኦሮሞና እንግሊዝኛ በተጨማሪ በሶማሊኛ ቋንቋ ለማስጀመር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ስለባንኩ እገዛ በሚሹ፣ስለ አገልግሎት አሰጣጥ፣ቅሬታና ግብረ መልስ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ወደ ግብይት ስርዓት ለማሳደግ በር ይከፍታልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረታዊ ነጥቦች መካከል የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማዘመን በመሆኑ ለዘርፉ ውጤታማነት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡