"የትሕትና ዕለት ፤ ጸሎተ ሐሙስ" - ኢዜአ አማርኛ
"የትሕትና ዕለት ፤ ጸሎተ ሐሙስ"

ሚያዚያ 13/2014/ኢዜአ/ "የትሕትና ዕለት ፤ ጸሎተ ሐሙስ"ጸሎተ ሐሙስ በዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ውስጥ ካሉት ቀናት መካከል አራተኛው ዕለት ነው።
ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር ማጠቡ ሲታሰብ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ባስተማረው ትሕትና ሰዎች በትሕትና ዝቅ ብለው ታናናሾችን እንዲመለከቱ ፣የተቸገሩትን እንዲጠይቁና እርስ በእርስ በመረዳዳት እንዲኖሩ ትምህርት የሚሰጥበት ነው።
ዕለቱ እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሠረት ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕጽበተ እግር፣ የምሥጢር ቀን፣የሐዲስ ኪዳንና የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
በስያሜዎቹ መሠረት በዚህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሎት ስለማድረጉ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ ማጠቡ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት ‹‹በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን›› በማለት የምዕመናን እግር ያጥባሉ ትምህርተ ትሕትናን በተግባር ያስተምራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ዕለቱ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቁርባን ስለመመሥረቱና እየሱስ ክርስቶስ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የሰው ልጅ ነጻነት ያገኘበት ነው ተብሎ ይታሰባል።
በጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ካከናወናቸው የሥረዓት ተግባራት በተጨማሪም በዕለቱ ትውፊታዊ ስርዓትን በጠበቀ ሁኔታ “ጉልባን” የተባለው ምግብ ይበላል።
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ሲሆን የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡
ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበርና ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል ይህምጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን መጠማት ያስታውሳል፡፡
ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
ምንጭ፡- የቤተክርስቲያኗ የስርዓት መጽሐፍትና፣ መጽሐፍ ቅዱስ