በኢትዮጵያ ዜጎች በነፃነት እንዲሰሩ ከለውጡ መሪዎች ጋራ እንሰራለን - አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዜጎች በነፃነት እንዲሰሩ ከለውጡ መሪዎች ጋራ እንሰራለን - አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2010 በኢትዮጵያ ዜጎች በፃነት እንዲሰሩ ከለውጡ መሪዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ገለጹ። አቶ አንዳርጋቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም ለንቅናቄው በተዘጋጀው የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላይ እንዳሉት፤ "በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ የሚደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም አለበት"። "ትግሉ ተጀመረ እንጂ አላለቀም ያሉት ዋና ፀሓፊው፤ ትግሉ የሚያበቃው የወጣቶች ሞት፣ እንግልት፣ እስራት ሲቆም፤ ዜጎች በአገራቸው በነፃነት ሰርተው መኖር ሲችሉ ነው" ብለዋል። በኢትዮጵያ ምድር እኩልነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ ከለውጡ መሪዎችና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ እንደ አቶ ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸውና ለማ መገርሳ ካሉ የለውጥ መሪዎች ጎን ሆነው በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል። መፈራራት፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ የሚኖርበት ጊዜ አብቅቶ ሁሉም ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መኖር የሚችሉበት ዘመን እንዲመጣ እታገላለሁ ሲሉም አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል። አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በተፈረደባቸው የአድልኦ ፍርድና በደረሰባቸው እስራት በእስር ቤት ሲማቅቁ ቆይተው ይህ የለውጥ መንግስት ባደረገው ምህረት ከእስር ቤት መውጣታቸው ይታወሳል።