የዓለም ዋንጫ አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ዋንጫ አዲስ አበባ ገባ

ግንቦት 16/2014/ኢዜአ/ በ2022 በኳታር የሚደረገው የዓለም እግር ኳስ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ በተለያዩ አገራት ለእይታ የሚቀርበው የዓለም ዋንጫ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
በተጨማሪም ብራዚላዊው የእግርኳስ ተጫዋች ጂሊያኖ ቤለቲ ዋንጫውን ይዞ ከመጣው ልዑክ ጋር አዲስ አበባ ገብቷል።
ባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ እና የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገዋል፡፡
በኳታር በሚካሄደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ የውድድሩ ዋንጫ በተለያዩ አገራት ለእይታ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ዋንጫው በዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያዋ መዳረሻ ሆናለች፡፡
ዋንጫው በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ከኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የዋንጫ ርክክብ መርሃ ግብር እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡
በነገው እለት በመስቀል አደባባይ እና በተመረጡ ቦታዎች ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ለእይታ እንደሚቀርብም ነው የተገለጸው፡፡
የዓለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡