በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በይፋ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት በይፋ ስራ ጀመረ

መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎት ይፋዊ ስራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄደ።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በአይነቱ ልዩ የሆነ የንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ ችሎትን አቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ችሎቱ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ፒያሳ የቀድሞው ብሪቲሽ ካውንስል ህንጻ ላይ ነው ስራ የጀመረው።
ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የንግድ፣ የባንክ፣ የኢንሹራንስ እና የኮንስትራክሽን የፍርድ ክርክሮች የሚስተናገዱበት ነው።
ከዚህ በፊት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ተደራጅተው ሲታዩ የነበሩ ጉዳዮችን በዘርፍ በመለየት ልዩ ችሎት መጀመሩም ለፍርድ ሂደቱ የራሱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሻናፊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የምድብ ችሎቱ በተለየ መልኩ ስራ መጀመሩ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ለሚነሱ የዳኝነት ጉዳዮች በተቀላጠፈ መልኩ ፍትህ ለመስጠት ያግዛል።
ይህም በአገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ አንዱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክ የንግድ ፍርድቤቶች በአገራት እንዲስፋፉ የሚጠይቀውን መስፈርት ለመመለስም የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ከተለያዩ የንግድ ነክ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ክርክሮች ምላሽ በመስጠት በዘርፉ የሚሰማሩትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ተመሳሳይ ምድብ ችሎቶች ለማስፋፋት በቀጣይ እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህ ለመጀመረው ምድብ ችሎት ልምድና ክህሎት ያላቸው ዳኞች በውድድር መመረጣቸውን ገልጸዋል።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉኣድ ኪያር በበኩላቸው ይህ ልዩ የሆነ ምድብ ችሎች ፍትህን በተቀላጠፈ ሁኔታ በመስጠት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል።
ምድብ ችሎቱ አምስት የንግድ፣ አምስት የባንክና ኢንሹራንስ እንዲሁም አንድ የኮንስትራክሽን ችሎቶችን በመያዝ በ11 ችሎት የተዋቀረ መሆኑን ገልጸዋል።
የምድብ ችሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ የአንድ መስኮት የዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው በዘርፉ ችሎት እንዲቋቋም ለረጅም ጊዜያት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲጠየቅ ለነበረው ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።