13ኛው የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ልማት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ  መስከረም 21/2011 በአፍሪካ ጥራት ያለው የስታቲስቲክስ መረጃን ለፖለሲ ግብዓትነት ለመጠቀም የህዝብና ቤት ቆጠራ አሰራርን ማዘመን ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር  ሙላቱ ተሾመ አስገነዘቡ። 13ኛው የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ልማት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በአህጉሩ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በወቅቱ፣ በጥራትና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ክፍተት እንዳለበት ይገለጻል። ክፍተቱን ለመሙላትም  የየአገራቱ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትና ልምድ የሚለዋወጡበት ሲምፖዚየም ተቋቁሟል። በሲምፖዚየሙ ላይ የአፍሪካ አገራት የስታቲስቲክስ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የብሄራዊ ካርታ ኤጀንሲ ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የጥናትና ምርምር ተቋማት እየተሳታፉ ነው። የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማም በአፍሪካ ደረጃ የህዝብና ቤት ቆጠራ ሳይቆራረጥ በየአስር ዓመቱ እንዲካሄድና የስታቲስቲክስ መስሪያ ቤቶች የአገራቸውን መንግሥት በማሳመን አስፈላጊውን በጀት ይዘው በትኩረት እንዲሰሩበት ለማስቻል ነው። ሲምፖዚየሙ ሲጀመር ዋናው ትኩረቱ  የህዝብ ቆጠራ ቢሆንም የኢኮኖሚ ስታቲስቲስክስ መረጃዎች በግዜና በጥራት ጎልብተው በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ነው። አገራቱ በ2020 የሚያካሂዱት የህዝብና ቤት ቆጠራ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግም የ13ኛው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ልማት ሲምፖዚየም ዋነኛ ትኩረቱ ነው። ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የህዝብና ቤት ቆጠራ አፍሪካ በ2030 እና አጀንዳ 2063 የጀመረችውን የልማት ውጥኖች ለማሳካት ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ከቆጠራው የሚገኘው ውጤት ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ ተግባራዊ ለማድረግና ቁጥጥር ለማካሄድ ወሳኝ ሚና እንዳለው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ለአገራቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። በአህጉር ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ጥራት ያለውና ወቅቱን የጠበቀ የስታቲሰቲክስ መረጃዎች ያስፈልጋሉ ሲሉም አመልክተዋል። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ አገራት መረጃዎችን ሲሰበስቡ፣ ሲተነትኑና ሲያከፋፈሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል። ከዚህ ባለፈም አጋራቱ በስታቲስቲክስ ላይ ያላቸውን አቅም በማሳደግ ከሀጉሪቱ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈለጉ መረጃዎችን በበቂ መጠን ተደራሽ ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉም መልዕክት አሰተላልፈዋል። የኢትዮያ መንግሥትም የስታቲስቲክስ መረጃ አስፈላጊነትን በመረዳት የአቅም ግንባታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል። ኢትዮጵያ አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መኗን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ቆጠራውን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የታገዘ ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል። የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር ሚሲተር ኦሊቨር ቺንጋያ በበኩላቸው በአህጉሩ ተዓማኒነት ያለው የስታቲስቲክስ መረጃ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት የልማት እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እንዳይካሄዱ አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ነው። በተለይ የኢኮኖሚ መረጃዎችንና ተዓማኒነት ማሳደግ አገራት የኢከኖሚ አማራጮችን እንዲያሰፉና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚኖራቸው ሽግግር ከፍ ያለ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። ሲምፖዚየሙ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ አኮኖሚክ ኮሚሽን ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም