ተከባብሮና ተሳስቦ አብሮ የመኖር ባህልን እናጠናክራለን ---የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

ጊምቢ ግንቦት 13/2010 በተቋሙ ያለውን ተከባብሮና ተሳስቦ አብሮ የመኖር ባህልን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የመጡ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች  ለኢዜአ እንዳሉት  በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ያለው አብሮነትና መተሳሰብ የሚያስደስት ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው የአርት ዲፓርትመንት ተማሪ መሀመድ ገላና በሰጠው አስተያየት በቅርቡ ስራውን የጀመረው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች በማሰባሰብ እያስተናገደ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ተማሪ መሀመድ እንደገለጸው ተቋሙ የወራት እድሜ እንዳለው ሳይሆን ረዥም ጊዜ የቆየ ያህል በተማሪዎች መካከል የሚታየው እርስ በርስ የመደጋገፍና ተግባብቶ የመኖር ባህሉ የሚበረታታ ነው። ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ያልተስተካከሉ አንዳንድ መሰረተ ልማቶችም እንዲሚሟሉ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቃል እንደተገባላቸውና ፈጥኖ ተግባራዊ  እንዲሆን የሚፈልጉ መሆናቸውን ጠቅሷል። የሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ተማሪ ሙኤን ዴንፓል በበኩሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድቦ በመጣበት ወቅት በደምቢዶሎ ህዝብ የተደረገላቸውን ቤተሰባዊ አቀባበል እንዳማይዘነጋው ጠቅሶ ግቢው ወስጥ ያለው ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህል አስደሳች መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው እስካሁን ባደረገችው ቆይታ ይበልጥ እንድትወደው ካደረጓት ውስጥ በተማሪዎች መካከል የሚታየው አንድነትና ተዋዶ የመኖር ባህል መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የህግ ተማሪዋ መዲና ገመቹ ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲውን ለመመረቅ ወደ ተቋሙ በመጡበት ወቅት እሳቸውን ለማየትና ንግግራቸውንም በአካል ለመስማት በመቻሏ መደሰቷን ተናግራለች፡፡ በተቋሙ ያለውን ተከባብሮና ተሳስቦ የመኖር ባህል በቀጣይም ተጠናክሮ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ በውጤታማነት እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ አዲስ የሆነው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መመረቁ በወቅቱ ተገልጿል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም