ለአካባቢው የዞን መዋቅር መፈቀዱ እንዳስደሰታቸው በሀላባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ሀዋሳ ህዳር  11/2011 መንግስት ላቀረቡት የመዋቅር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዞን እንዲሆኑ መፍቀዱ እንዳስደሰታቸው በሀላባ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ለዞኑ ልማት ተገቢውን ድጋፍ   እንደሚያደርጉ ነዋሪዎቹ  ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አቡካ ያሲን እንዳሉት በልዩ ወረዳ ይተዳደር የነበረው ሀላባ ዞን መሆኑ ከቀድሞ የተሻለ ጠቀሜታ አለው፤ የመሰረተ ልማት ተቋማት ለማሰፋፋት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ "ለዞኑ ልማትም የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ከሚሾሙ አካላት ጋር በመተባበር በጋራ እንድንሰራ ያነሳሳናል" ብለዋል፡፡ ሌላው ነዋሪ አቶ ኬይሩ ሁሴን በበኩላቸው የዞን ጥያቄው መመለሱ ቀደም ሲል ከነበረው አወቃቀር በተሻለ የመሰረተ ልማት ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ከርቀት የሚመጡ ነዋሪዎችም ቅርብ የሆነ የመንግስት አስተዳደር እንደሚያስገኝላቸው ተናግረው በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የዞን ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ለከተማዋ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቃሲም ሀሰን ናቸው፡፡ "በርካታ ስራ አጦችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል፤ ብዙ ልማትም ይኖራል፤ ይህም በጣም ያስደሰተኝ ነው" ብለዋል፡፡ የልማቱን አባቶችን የማበረታታትና ከጎናቸው መቆም ከእሳቸው እንደሚጠበቅ ገልጸው ህብረተሰቡም ወደ ልማት እና  ወደ መደመር መምጣት እንደሚኖርበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሙና በሰጡት አስተያየት "ዞን መሆኑ ብዙ ነገር ይለወጣል፣ የተለያዩ ቢሮዎች ይከፈታሉ፣ የከተማውም ህብረተሰብ ጭምር ተጠቃሚ ይሆናል ከተማዋም ታድጋለች፤ የስራ እድልም ይከፈታል" ብለዋል፡፡ አካባቢው ከልዩ ወረዳ ደረጃ ወደ ዞን ማደጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከመንግስት ጎን በመቆም ልማትን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡ ሌላው በንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት ነጂብ ሼህሱሊ በበኩሉ ቀደም ሲል በቀበሌ ደረጃ የነበሩት በሀላባ ጫፍ ላይ የሚገኙ አካባቢዎች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም እስከ ሀላባ ከተማ ድረስ ለመጓዝ እንደሚገደዱ ተናግሯል፡፡ "አሁን ወረዳ መሆን በመቻላቸው የሚፈልጉትን ጉዳይ በቅርበት ማግኘት ያስችላቸዋል" ብሏል፡፡ መዋቅሩ በመፈቀዱ የመሰረተ ልማት ተቋማት ከማስፋፋት ባለፈ  በዞን ደረጃና በልዩ ወረዳ ደረጃ ያለው እኩል ስላልሆነ የአሁኑ ከፍተኛ እድገትን ማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ በግሉ የንግድ ስራውን ለማስፋፋትና የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም