የወጣቶችን ስብዕና ለመገንባት የሁሉም ድጋፍ ተጠየቀ

አዳማ ታህሳስ 13/2011 መጤ ልማዶችና አደንዛዥ ዕጾችን በመከላከል የወጣቶችን ስብእና ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። ሚኒስቴሩ ወጣቶችና ታዳጊዎች በስነምግባር የታነፁና ስብእናን የተላበሱ እንዲሆኑ በቅንጅት ለመስራትና  ለአዎንታዊ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱ ይታወቃል። እቅዱን ለመተግበር በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010 ዓም የተቋቋመው ግብረ ኃይል ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ተግባራት ገምግሞ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ዛሬ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንደገለፁት ከአገሪቱ ህዝብ ብዛት አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ታዳጊ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ካላቸው ከፍተኛ ቁጥር ባሻገር፤ የእምቅ አቅም ፣ ብሩህ አእምሮና ተስፋ ባለቤት በመሆናቸውና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠርና የመቀበል ካላቸው ብቃት ጋር ተዳምሮ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ማህበራዊ ልማት፣ ፖለቲካዊ መረጋጋትና ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከከተሜነት መስፋፋትና በባህል ወረራ ምክንያት እየተስፋፉ ያሉት አሉታዊ መጤ ልማዶች ፣ የአደንዛዥ እፆችና አደገኛ መድሃኒቶች ዝውውር ሁሉንም ለማወቅ ጉጉት ባላቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች ስብእና ግንባታ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ወጣቶች አገራቸውን ለመረከብ በቂ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወሳኝ እድሜአቸው ላይ ለተለያዩ ሱሶች እየተጋለጡ፣ ራዕይ አልባ እየሆኑና ምርታማነታቸው እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል። ቁጥራቸው የማይናቅ ወጣቶች ለመጤ ልማዶች ፣ ለአደንዛዥ ዕፆችና አስተሳሰቦች ሲጋለጡና ከማህበረሰባቸው ባህልና ሞራል ጋር የሚጣረሱ ድርጊቶች ሲፈፅሙ ይስተዋላል ሲሉም ተናግረዋል። የዚሁ ውጤት ደግሞ በበአገሪቱ የሚገኙ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስሮች እንዲላሉና እንዲሸረሸሩ ፣የእምነት ስርዓቶች እንዳይከበሩና አገር በቀል እውቀቶች እንዲዳከሙ እያደረገ ነው። ጠቃሚ ባህሎችና ልማዶችን ለትውልድ ማስተላለፊያ ስርዓቶችንና ማህበራዊ የመደጋገፍና የመረዳዳት ልምዶች በግለኝነት አስተሳሰብ ምክንያት ለከፍተኛ አደጋ እንዲጋለጡ ማድረጉን ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል። ይህንኑ በመቀልበስ በወጣቶችና በታዳጊዎች ስብእና ግንባታ ላይ በተቀናጀ መልኩ የጋራ ርብርብ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል። የህክምና ፣ የስነ ልቦናና የስነ መለኮት ባለሙያ ዶክተር ወዳጄነህ መሀረነ በበኩላቸው የወጣቶችና የታዳጊዎች ስብእና መገንባት ጉዳይ አገራዊ ንቅናቄ የሚያስፈልገው የሁሉም ወገን ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት፣ አርአያ የሆኑ ታዋቂ ሰዎች፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች በሙሉ  አቅማቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በምክክር መድረኩ ላይ በአደንዛዥ ዕፆች የቅድመ መከላከልና የማገገሚያ አገልግሎት ዙሪያ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምርጥ ተሞክሮ በመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ በአቶ ዘላለም ይትባረክ አማካኝነት ቀርቧል። በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው የነበሩና በማገገሚያ ማዕከሉ ድጋፍ አግኝተው ከሱስ ነፃ የሆኑ  ሁለት ወጣቶች በመድረኩ ላይ ተገኝተው ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም