በግላኮማ ምክንያት በዓይን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የአይን ግፊትን መለካት ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በግላኮማ ምክንያት በዓይን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የአይን ግፊትን መለካት ያስፈልጋል ተባለ

መጋቢት 22/2011 በግላኮማ ምክንያት የሚደርሰውን የአይን ብርሃን ማጣትን ለመከላከል የአይን ግፊትን በየጊዜው መከታተል እንደሚገባ ነው የግላኮማ ስፔሻሊስት የተናገሩት።
የግላኮማ ስፔሻሊስትና በአዲስ አባባ የኒቨርሲቲ የአይን ህክምና መምህርት ዶክተር አበባ ተክለ ጊዮርጊስ እንደተናገሩት ግላኮማ በጊዜ ታክሞ መዳን ካልቻለ በዚህ ምክንያት የሚመጣውን የአይን ብርሃን ማጣት በህክምና መመለስ አይቻልም ፡፡
ግላኮማ ከአይን ህመሞች አንዱና ብዙ ጊዜም ከአይን ግፊት መጨመር ጋር ይያያዛል ያሉት ዶክተር አበባ የግፊቱ መጨመር ነርቭን በመጉዳት የእይታ አድማስን እያጠበበ ቀስ በቀስ ለአይነስውርነት ይዳርጋል ብለዋል፡፡
ዶክተር አበባ እንደገለፁት የአይን ግፊት ከ20 በታች ሲሆን መጠነኛ መሆኑና ከዚያ በላይ ሲሆን ግን ግፊቱ ነርቮችን የሚጎዳበት ሁኔታ ይፈጠራል።
“አንድ ሰዉ የአይኑ ግፊት 20 ሆኖ ህክምና ካላደረገ የአይን ግፊቱ እየጨመረ በመሄድ ብርሃኑን ለማጣት እስከ 15 አመት ሊወስድበት ይችላል” ያሉት ዶክተሯ የአይን ግፊቱ ከ30/40 እየሆነ ሲሄድ ብርሃን ማጣት በዛው ልክ ይፈጥናል ብለዋል፡፡
እድሜው 40 እና ካዛ በላይ የሆነ ሰው፣ በቤተሰብ ግላኮማ ሲኖር፣ የአይን አለርጂክ መድሃኒቶችን( ስቴሮይድ) በብዛት መጠቀምና የሞራ ግርዶሽ በግዜ ካልታከመ ግላኮማ በመፍጠር እይታን የሚያሳጡ ሁኔታዎች መሆናቸውንም ነው የገለፁት ፡፡
“አብዛኛው የግላኮማ አይነት ስሜት የለውም፣ ይህም ሰራቂ ብርሃን ያስብለዋል” ያሉት ዶክተሯ ሰዎች ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ አንድ አይናቸው ወይም ሁለቱም ከተጎዳ በኋላ ወደ ህክምና የሚመጡበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ የግላኮማ አይነት በተለይ ሴቶች ላይ በሚታየው ምልክት አይን ይቀላል፣ ያማል ፣ብርሃን ይፈራል፣ራስምታት ይኖራል በተጠቃው የአይን ክፍል በኩልም 40/50 የሆነ የአይን ግፊት ከታየና ቶሎ ካልታከሙ አይን የሚጠፋበት ሁኔታ እንዳለ ተናግራዋል፡፡
ህፃናት ላይ የሚያጋጥመው ግላኮማ ማንም ሰው ሊለየው በሚችል መልኩ የሚከሰት መሆኑን የገለፁት ዶክተሯ ከተወለዱ የመጀመሪያ ስድስት ወር ላይ የሚታይና እስከ አንድ አመት ደግሞ በደንብ እንደሚያስታውቅ ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት ሁለቱም አይን አልያም አንዱ የአይን ኳስ ትልቅ ይሆናል፣ መስታወቱም ጉም ለብሶ ብርሃን የመፍራትና የታመመው አይን የማልቀስ ሁኔታ ይታይበታል ብለዋል፡፡
የህፃናት አይን ላይ ለውጥ ሲታይ ወላጆችና አሳዳጊዎች በተፈጥሮ ትልልቅ አይኖች ናቸው ብለው መቀበል የለባቸውም ያሉት ዶክተሯ እንደ ችግር አይተው ወደ ህክምና መውሰድ እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡
ግላኮማ ያጋጠማቸው ህፃናት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ላይ ተገቢውን ህክምና ካገኙ እንደሚድኑም ነው የተናገሩት፡፡
አንድ ሰው ግላኮማ እንዳለበት ለማወቅ በመመርመር ብቻ ችግሩን ማወቅ እንደሚችል ገልፀው የአይን ግፊትን በየአመቱ መመርመር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከ13አመት በፊት በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ 65 ሺህ ሰዎች በግላኮማ ምክንያት የአይን ብርሃናቸውን እንዳጡ ማመልከቱን የሚናገሩት ዶክተር አበባ ከዛ ወዲህ ቁጥሩ ልጨምር እንደሚችል ገልጸው በቀጣይ አመትም በዚሁ ዙሪያ የሚሰራ ጥናት ይኖራል ብለዋል፡፡
የግላኮማ ህክምና የህመሙን ደረጃ ባለበት ማቆም መሆኑን የገለፁት ዶክተሯ “በቀጣይነት እይታን እንዳናጣ እድሜ ልክ ሳይቋረጥ ክትትል ማድረግ እንጂ የተጎዳውን መመለስ አይቻልም” ብለዋል፡፡
በተለይ በየገጠሩ የግላኮማ ህመሙ ተባብሶና የመጨረሻ ደረጃ ደርሶ ወደ ህክምና እንደሚመጡ ያወሱት ዶክተሯ በሃገሪቱ የሞራ ግርዶሽ በዘመቻ እየተሰራ በመሆኑ የግላኮማን ደረጃ በተጓዳኝ ልየታ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የግላኮማ ህክምናና ኦፕሬሽን ልምድ ባላቸውና በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አበባ በኢትዮጵያ በዚሁ ዘርፍ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ስድስት ሃኪሞች ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መድሃኒቶቹን በሀገር ውስጥ ማምረት አለመጀመሩም ገበያ ላይ ያለማግኘት ችግርና አቅምን የሚፈታተን መሆኑን ተናግረዋል።
“አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግላኮማን በሰብ ስፔሻሊቲ ለማሰልጠን እየተሰራበት ነው፤ ከተሳካልን በቀጣይ አመት እንገባበታለን” ያሉት ዶክተር አበባ ይህም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በመጨመር አገልግሎቱን በጥራት ለማዳረስ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
አቶ ውብአለም ጌታቸው የግላኮማ ህመም አጋጥሟቸው ሚኒሊክ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ነው ያገኘናቸው።
ህመሙ ሲጀምራቸው በአይናቸው ላይ ጉም መሰል ነገር ታይቷቸው እንደነበር አስታሰው ተከታታይ ምርምራ በማድረግ የአይናቸው የጤንነት ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አንድ አይናቸውን ኦፕራሲዮን እንደተደረጉና ለሁለተኛውም ክትትል እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው “እይታዬን ላለማጣት ከሃኪም መራቅ የለብኝም የሚል ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ “ብለዋል፡፡
የአይን ግፊታቸውን በየጊዜው እየተከታተሉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ውብአለም ጥሩ የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ ማህፀንተ ዝርጎ ግላኮማ እንዳለባቸው ካወቁ 9 አመት እንዳስቆጠሩ ገልፀው ከብዙ ምርመራ በኋላ አንድ አይናቸውን ኦፕራሲዮን እንዳደረጉና በየጌዜው ለአይናቸው ጤንነት ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሚደረግላቸው የህክምና ክትትል ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት ወይዘሮ ማህፀንተ በየጊዜው የመድሃኒቶች ዋጋ ማሻቀብ ግን እንዳስመረራቸው አልሸሸጉም ፡፡