ቻይና የዓለም አየር ብክለትን ለመቆጣጠር ጥረት አደርጋለሁ አለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና የዓለም አየር ብክለትን ለመቆጣጠር ጥረት አደርጋለሁ አለች

ግንቦት 28/2011 ቻይና የዓለም አየር ብክለትን ለመቆጣጠር ዓለም አቀፍዊ ጥረት እንደምታደርግ ገለጸች።
አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን "የአየር ብክለትን እንዋጋ" በሚል መሪ ቃል በቻይና መከበሩን ሲ ጂ ቲኤን በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ይህ የአካባቢ ጥበቃ ቀን በምስራቅ ቻይናዋ ግዛት ሃንግዡ ከተማ እንደተካሄደ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ቻይና የአካባቢ ጥበቃ ቀንን እ.አ.አ በ1993 በቤጂንግና በ2002 በሸንዘን ከተሞች ለሁለት ጊዜ ያክል ያከበረች ሲሆን ይኸኛው በሃንግዡ ከተማ የሚከበረው ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በአለም ዙሪያ ያሉ ባለስልጣናት፣ ምሁራንና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ጭምር በመሰባሰብ ስለ አየር ብክለት ግንዛቤ በመፍጠርና ችግሩን ለመቅረፍም ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአካባቢ ጥበቃ ቀንን አስመልክቶ በላኩት መልዕክት፤ ማንኛውም ግለሰብ፣ ድርጅትና ሃገር የአየር ብክለት እያስከተለ ያለውን ጉዳት ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ሊከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
90 ከመቶ በላይ የዓለም ህዝብ ጤነኛ አየር እንደማያገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልፆ ሰባት ሚሊዮን የአለማችን ሰዎች በመጥፎ አየር ምክንያት ያለግዜያቸው እንደሚሞቱም ተነግሯል፡፡
ከዓለም አቀፉ የአካባቢ ቀን በተጨማሪ እ.አ.አ ከሰኔ 2-5/2019 ድረስ ባሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የቻይና አለምቀፍ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ትብብር ተካሂዷል፡፡
በዚህ ሁነት ላይም ስለ አለማቀፍ አስተዳደርና የስነ-ምህዳር ስልጣኔ፣ የአረንጓዴ ልማትና ዘላቂነት ያለው ልማት፣ ፈጠራ፣ አስተማመኝ ምርትና ፍጆታ፣ ታዳሽ ኃይል፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ በውይይቱ የተመከረባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን በማጠቃለያ ዘገባው አስፍሯል፡፡