የአፍሪካ ዋንጫ ድባብና የማየት ፍላጎት በኢትዮጵያ በሚገኘው የስፖርቱ ተመልካች ዘንድ ለምን ተቀዛቀዘ? - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ ድባብና የማየት ፍላጎት በኢትዮጵያ በሚገኘው የስፖርቱ ተመልካች ዘንድ ለምን ተቀዛቀዘ?

ሰኔ 30/2011 (ኢዜአ)32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግብጽ አስተናጋጅነት ከሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ ከተጀመረ 16 ቀናትን ያስቆጠረ ቢሆንም በኢትዮጵያ እንደ ሌላው ጊዜ ጨዋታውን በጉጉት ጠብቆ የማየቱም ሆነ የመከታተል ፍላጎትና መነጋገሪያነት ተቀዛቅዞ ታይቷል። ኢዜአ የአፍሪካ ዋንጫ ድባብና የማየት ፍላጎት በኢትዮጵያ በሚገኘው የስፖርቱ ተመልካች ዘንድ ለምን ተቀዛቀዘ? ለመቀዛቀዙስ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? በሚለው ጉዳይ የስፖርቱ አፍቃሪዎችንና እና የስፖርት ጋዜጠኛን አነጋግሯል። ሚካኤል ደበበ የአፍሪካ ዋንጫን መከታታል የጀመረው እ.አ.አ በ1982 በሊቢያ አስተናጋጅነት በተካሄደውና የጋና ብሔራዊ ቡድን አሸናፊ ከሆነበት 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አንስቶ ነው። በተመለከታቸው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች የካሜሮንና የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በዋንኛነት እንደሚመለከትና ከካሜሮን በኩል ሮጀር ሚላና ሪጎበርት ሶንግ ከናይጄሪያ ራሺድ ያኪኒና የጄጄ አኮቻ አድናቂ እንደነበር ያስታውሳል። ሚካኤል የአፍሪካ ዋንጫ መመልከት በጀመረበት እና አሁን ያለውን ድባብ ፍፁም የተለያዩ መሆኑን በመግለፅ የተለያዩ ምክንያቶችንም ያነሳል። አሁን የአፍሪካ ዋንጫ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የሴቶች የዓለም ዋንጫ፣ ኮፓ አሜሪካ እና ሌሎች ውድድሮች መካሄዳቸው አፍሪካ ዋንጫው ትኩረት እንዳያገኝ እንዳደረገ ገልጿል። ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ አለመሳተፏ የአፍሪካ ዋንጫን እኔን ይወክለኛል ብሎ ህብረተሰቡ የማየት ፍላጎቱ እንዲቀዛቀዝ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል። በኢትዮጵያ አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ለድባቡ መቀዛቀዝ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ነው ሚካኤል የሚናገረው። የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመለከተው ከታች ጀምሮ በመስራት ለአፍሪካ ዋንጫ ብቁ የሆነ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደሚያስፈልግና ለዚህም የስፖርቱ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጿል። ሌላኛው የእግር ኳስ አፍቃሪ ታታ መሐመድ የአፍሪካ ዋንጫን ጊዜው በትክክል ባያስታውሰውም ከ20 ዓመት በፊት የአፍሪካ ዋንጫን መከታታል እንደጀመረ ያስታውሳል። የአፍሪካ ዋንጫን መመልከት በጀመረበት ጊዜ ህብረተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀውና የሚመለከተው ውድድር እንደበርም ነው የገለጸው። አሁን የአፍሪካ ዋንጫ ሌሎች ውድድሮች በመኖራቸው እሱና ጓደኞቹ የአፍሪካ ዋንጫን አጀንዳ አድርገው እንደማይወያዩበት ገልጿል። የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድበት ጊዜ መቀየሩ ውድድሩ ትኩረት እንዳያገኝ እንዳረገውም ይናገራል። በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 24 ከፍ ማለቱ ውድድሩን አሰልቺና ተመልካቹ ጉጉቱን እንዲቀነስ ማድረጉን ገልጿል። አቶ ፋንታሁን ሃይሌ በመጽሐፍ ስማቸው 'አስኳል' የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በአጀንዳና በስፖርት አምድ የተለያዩ ጽሁፎች በመጻፍ በመስራት ላይ ይገኛሉ። አቶ ፋንታሁን እ.አ.አ በ1976 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ የአፍሪካ ዋንጫን መመልከት እንደጀመሩና እ.አ.አ በ1986 ግብጽ ካስተናገደችው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመዞር ውድድሩን ማየት እንደቻሉም ያስታውሳሉ። የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት በነበራቸው ትጋት የአፍሪካ ዋንጫ የእድሜ ልክ መግቢያ እንደሰጧቸውና በዛም በአፍሪካ አገራት እየዞሩ ውድድሩን መመልከታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል። በወቅቱ የነበሩ ነባር ጋዜጠኞች የአፍሪካ ዋንጫን አስመልክቶ ያደረጉት የነበረውን ዝግጅት አቶ ፋንታሁን እንዲህ ያስታውሳሉ። የነበረው ቅስቀሳ ህብረተሰቡ የአፍሪካ ዋንጫን በጉጉት እንዲጠብቅ ያደርገው ነበር ሲሉ ገልጸዋል። አሁን የአፍሪካ ዋንጫ ህዝቡ በትኩረት እንዲታይ ያላደረገውና የቀዘቀዘው የስፖርቱ አፍቃሪ በአገሩ እግር ኳስ ላይ ተስፋ መቁረጡ እንደሆነ ተናግረዋል። በአገር የውስጥ የሊግ ውድድሮች የሚታዩ ብጥብጦች እና የእግር ኳሱ ደካማ መሆን እንዲሁም የእግር ኳስ አፍቃሪው የስፖርት ቤተሰቡ የአፍሪካ ዋንጫን እንዳይመለከት ያደረጉት ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ከሚቀርባቸው የአገራቸው እና የአፍሪካ እግር ኳስ ቀድመው ስለ አውሮፓና አሜሪካ እግር ኳስ ትኩረት መስጠታቸው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ትኩረት እንዳያደርግ አድርጎታል ብለዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ችግሮች በአደረጃጀትና በመዋቅር ማስተካካያ እየተስተካከሉ ከመጡ ህብረተሰቡ የአፍሪካ ዋንጫን ብቻ ሳይሆን የአገሩን እግር ኳስ የማየት ጉጉቱ እንደሚጨምር ተናግረዋል። ስፖርቱን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች የአገራቸውን እና የአህጉራቸውን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው መዘገብ እንዳለባቸው ይገልጻሉ። 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአሁኑ ሰአት ለሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ጨዋታዎች እየተደረጉ ሲሆን ውድድሩ ሐምሌ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል።