በደቡብ ክልል የጸጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል....ኮማንድ ፖስት - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል የጸጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል....ኮማንድ ፖስት
ሐምሌ 24/2011 በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ኮማንድ ፖስት አስታወቀ። የኮማንድ ፖስቱ አካላት ዛሬ የክልሉን የጸጥታ ጉዳይ እስመልክቶ በሃዋሳ ከተማ ለጋዜጠኞች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል ፡፡ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ እዝ ዋና አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሜጀር ጄኔራል ሙዘይ መኮንን እንዳሉት በክልሉ ከመደራጀት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሃዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን ወረዳዎች ላይ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። በእዚህ የተነሳ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥራ ፀጥታውን ማስጠበቅ ባለመቻሉ ሕግን ለማስከበርና የህዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ ሲባል የክልሉ ፀጥታ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ቀደም ሲል ከነበሩ ስጋቶች የተነሳ በጥምር ኮሚቴ ሲመራ እንደነበር የገለጹት ዋና አዛዡ፣ በእዚህም በሃዋሳ ከተማ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ማስቀረት ቢቻልም ብዙ ዝግጅት ባልተደረገባቸው የሲዳማ ዞን ወረዳዎች ላይ በህዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል ፡፡ ይህም ሆኖ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ሠራዊት በመመደብ የመከላከል ሥራ መሰራቱን ነው የገለጹት ፡፡ የክልሉ ፀጥታ በኮማንድ ፖስት መመራት ከጀመረ በኋላ ሁሉም የፀጥታ አካላት በተጠናከረ መልኩ በቅንጅት እየሠሩ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት መሻሻሎች መታየታቸውንና በአጭር ጊዜ ውስጥ የኮማንድ ፖስቱ ሥራ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሠራዊቱ አባላት ከአምስት ቀናት በፊት የነበረውን የሠላም ማስከበር እንቅስቃሴያቸውን በመቀነስ በካምፕ በመቆየት የፓትሮል ሥራ ብቻ እያከናወኑ እንደሚገኙም አመልክተዋል ፡፡ እንደ ሜጀር ጄኔራል ሙዘይ ገለጻ በየአካባቢው ያለው ህብረተሰብ ተጠርጣሪዎችን አጋልጦ በመስጠት ለፀጥታው ኃይሉ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ፡፡ የክልሉ ፀጥታ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ የተደረገው መደበኛ ህጎችን ለማስከበር መሆኑን ጠቁመው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ኮማንድ ፖስቱ ተወያይቶ በጊዜያዊነት ከሚያግዳቸው እንቅስቃሴዎች ውጭ ምንም አይነት ክልከላዎች እንደሌሉም ተናግረዋል ፡፡ የደቡብ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ኑሪዬ ሱሌ በበኩላቸው ያልተፈቀደ ስብሰባና ሰልፍ እንዲሁም በሕገ-መንግስታዊ ሥርዐቱና በዜጎች ሰብዐዊ መብቶች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ፤ ቅስቀሳቀዎችና ግንኙነቶች በመደበኛ ህጉም ላይ የተከለከሉ በመሆናቸው ኮማንድ ፖስቱ እነዚህን ለማስከበር እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ የታወጀው ኮማንድ ፖስት እንጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለመሆኑ በዜጎች ሰብዐዊ መብቶች ላይ ምንም አይነት እገዳ እንዳልተጣለም አስታውቀዋል ፡፡ አክለውም “በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ተጠያቂ ከማድረግ አንፃር ሀዋሳን ፣ ይርጋለምንና አለታ ወንዶን ማዕከል ያደረጉ የምርመራ ቡድኖች ተቋቁመው የተጠናከረ ምርመራና ክስ የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ነው” ብለዋል ፡፡ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የገለጹት። በሀዋሳ አካባቢ ባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ የተገደበው ተሽከርካሪዎቹ በወቅቱ የወንጀል ድርጊትን ለማባባስ ከነበራቸው ሚና የተነሳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል ናቸው ፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ሥጋት ሊሆኑ በሚችሉባቸው በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም እንደዚሁ ኮማንድ ፖስቱ ገምግሞ ካመነበት የሁለት እግር ሞተር እንቅስቃሴን ሊገደብ እንደሚችል ተናግረዋል ፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚገኙ የተናገሩት ኮሚሽነሩ በዚህ ውስጥ የህብረተሰቡ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ሕግ ከማስከበር ሥራው ባሻገርም ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን የመቆጣጠርና ከሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የፀዱ ከተሞችን የመፍጠር ተግባር በተደራጀ ሁኔታ እንደሚያከናውንም ተናግረዋል ፡፡