ኢትዮጵያ የዓለም ስራ ድርጅት ስምምነትን እንድታጸድቅ ተጠየቀ

መስከረም 30/2012 የቤት ሰራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የዓለም ስራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 198ን እንድታጸድቅ በምስራቅ አፍሪካ የዓለም ሰራተኞች ፌዴሬሽን ጠየቀ። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ከዓለም አቀፉ ሰራተኞች ፌዴሬሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለቤት ሰራተኞች ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እያካሄደ ይገኛል። ለሁለት ቀናት የሚቆየው የምክክር መድረክ በቤት ሰራተኞች መብት አከባበር ላይ ሰፊ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ፌዴሬሽን የቤት ሰራተኞች የሚደርስባቸውን ችግር ለመከላከል የዓለም ስራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 198 ፀድቆ ስራ ላይ እንዲውል አድርጓል። ኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞችን መብት ለማስከበር የወጣውን ስምምነት እስከ አሁን ድረስ የአገሪቱ ህግ ሆኖ በስራ ላይ እንዲውል አላጸደቀችም። በምስራቅ አፍሪካ የዓለም አቀፉ ሰራተኞች ፌዴሬሽን አስተባባሪ ቪኪ ካኒዮካ እንደገለጹት፤ የቤት ሰራተኞች ለኢኮኖሚ ዋስትና መሰረቶች ስለሆኑ መብታቸው ሊከበር ይገባል። በተለይም በቤት ወስጥ ህጻናቶችንና አቅመ ደካማ አዛውንቶችን በመንከባከብ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። ሆኖም ግን በአብዛኛዎቹ አገሮች ያሉ የቤት ሰራተኞች የሚሰጡትን አገልግሎት የሚመጥን ደመወዝ፣ አስፈላጊው የህግ ከለላና ጥበቃ እንደማይደረግላቸው አስረድተዋል። በዓለም ላይ ከ67 ሚሊዮን በላይ የቤት ሰራተኞች የሚገኙ ሲሆን 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የቤት ሰራተኞች በተለያዩ መንገድ የሚደርስባቸውን በደል ለመከላከል ኮንፌዴሬሽኑ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የቤት ሰራተኞች ማህበር የተቋቋመ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭ በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት የሚሰሩ ሴቶች መብታቸው ለማስከበር ማህበር ማቋቋማቸውን ጠቁመዋል። ኮንፌዴሬሽኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ የቤት ሰራተኞች ለመብታቸው መታገል እንዲችሉ ማህበር እንዲያቋቁሙ እየሰራ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። መንግስት የዓለም ስራ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 198 እንዲያጸድቀውና የቤት ሰራተኞችን መብት ለማስጠበቅ አሰሪዎች፣ ሰራተኞችና የሚመለከታቸው አካላት ውይይት የሚያደርጉበት አገር አቀፍ የአማካሪ ቦርድ መቋቋሙን አመልክተዋል። የዓለም ስራ ድርጅት ከ55 አገሮች የተውጣጡ ከ600 ሺህ በላይ አባላት አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም