አየለ ያረጋል- ኢዜአ የጥበብ ድባብ በድባብ መናፈሻ ግቢ ሰፍኗል።በደማናማው ምሽት ባለዜማ ጉርምራም ያስተጋባል፤ ካፊያ ያረሰረሳቸው ማራኪ ዛፎች ጠፈጠፍ ቁልቁል ይቸፈችፋሉ፤በባለ ግርማ ሞገሱ በር የሚወጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ መናፈሻው ይተማሉ። ከዛፎች ስር የተጠለሉ ሰዎች በጽሞና ድባብ ጎራማይሌውን ትዕይንቱን ይታዘባሉ። እኔም ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ድባቡን በሰዓሊ፣ በደራሲ፣ በድምጻዊ፣ በዳይሬክተር….. በሌሎችም ጠቢባን ዓይንና አዕምሮ አሰብኩት። ስድስት ኪሎ (ዩኒቨርሲቲው) ፊት ለፊት ካለው የድባብ መናፈሻ ነኝ፤ የ‘ጥበብ በአደባባይ’ መክፈቻ ዝግጅት ታድሜ። አዲስ አበባ ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች አሏት፣ ለፈጠራም የምታነሳሳ የደራች ከተማም ናት። 'ጥበብ በአደባባይ'ም የአዲስ አበባን ኪናዊ ገጽ ወይም ደግሞ ጥበባትን ከባህል ማዕከላት ወደ ከተማዋ ሕዝብ መገናኛ ጎዳናዎች ማድረስ ነው፤ ወደ ሰዎች የዕለት ከዕለት ኑሮ የሚያደርስ ፌስቲባል። ‘ጥበብ በአደባባይ’ በጀርመን የባህል ማዕከል (ጎተ ኢንስቲትዩት) ሃሳብ አመንጭነት ባሳለፍነው ዓመት ተጀመረ። በመርሐ ግብሩ ሕዝቦች በበርካታ ጥበባዊና ባህላዊ ክንውኖችን በአዲስ አበባ አደባባዮች ይሳተፋሉ። ይህም ሕዝቡ ጥበብን ፈልጎ ከመሄድ ይልቅ ጥበብ ራሷ አላፊ አግዳሚ አዲስ አበቤን ጠርታ ግብሯን እንድታበላ የሚያደርግ ግብ የሰነቀ ፌስቲቫል ነው። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዝግጅቱ ትናንት ማምሻውን በይፋ ተከፍቷል። ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ቆይታም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ይቆያል። በጀርመን ባሕል ማዕከል (ጎተ) ዳይሬክተር ዶክተር ጁሊያ ሳትለር ለኢዜአ በሰጡት አስተያይት “ማዕከላችን ለጥበብ ይተጋል፤ በዚህም ከጥበብ አጋሮቻችን ጋር በመመካከር ጥበብ በአደባባይን አዘጋጅተናል። ሰዎችን ማግኘት፣ መተዋወቅና መስተጋብራችን ማጠናከር ስለምንፈልግ ነው” ይላሉ። ኢትዮጵያዊያን ለጥበብ ያላቸው ፍላጎት፣ የፈጠራ አቅምና ተሰጥኦ ከፍተኛ ነው የሚሉት ዳይሬክተሯ “አብሬ በመስራቴም ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል። ባለፈው ዓመት የነበረው የሶስት ሳምንት ቆይታ ቅቡልነቱና የሕዝቡ ተሳትፎ አስደሳች እንደነበር ይናገራሉ። ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች 'ጥበብ በአደባባይ'ን መታደማቸውን አስታውዋል። እናም ዘንድሮ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ አምስት ዋና ዋና ስፍራዎች/አደባባዮች አስራ አንድ የተለያዩ ጥበብና ጨዋታዎችን ይዞ መቅረቡን ተናግረዋል። መገናኛ፣ መስቀል አደባባይ፣ ቦሌ መድሃኒያለም፣ ብሔራዊ ትያትር፣ 6 ኪሎ የተመረጡ ስፍራዎች ናቸው። የሰርከስ ጉዞ፣ ሲኒማኛ ይናገራሉ? (የፊልም ቀረጻ፣ ትወና፣ ዳይሬክቲንግ)፣ ጓዳና ጎዳና (በኪነ ህንጻ ጥበብ)፣ የከተማ ሱቅ (ቤቶችና ከተማ ዲዛይን አንጻር)፣ ፎቶ ቀጭ ቀጭ ( የፎቶ ጥበብ)፣ ትንሿ የፈጠራ ማዕከል (የስዕል ጥበብ)፣ ተጫወች አዲስ አበባ፣ ሙዚቃ ግቡበት (የሙዚቃ ክዋኔዎች)፣ እንቅመስ (ጥበብን ማጣጣም)፣ ፀሀይ (በንባብ ዙሪያ ላይ)ና ስነ ጽሁፍ በመርሐ ግብሩ የታቀፉ ዝግጅቶች ናቸው። ከነዚህ የተለዩ የጨዋታና ጥበብ ፌስቲቫሎችን አስመልክቶ አስተያይታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጥበብ አዘጋጆችም ይገኛሉ። አርቲስት አስቴር በዳኔ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ አዘጋጅ ናት። 'ጥበብን የምናገኛት በአራት ማዕዘን ክፍል ውስጥ ታጥራ ነበር' የምትለው አስቴር ጥበብን በአደባባይ ግን ጥበብን ወደ ህብረተሰቡ ይዞ መዝለቁን ትናገራለች። በስነ ጽሁፉ ዘርፍ በጾታ፣ በዕድሜና በአመለካከት የተለያዩ ሰዎች እንደሚሳተፉ ትናገራለች። “ለሁሉም የሚሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሰዎች አመለካከታቸውን በጥቅስ መልክ ይጽፋሉ፤ ጅምር ሃሳብ እሰጣቸዋለሁ፤ ያን ጨርሰው ይጽፋሉ። በነጻ አንደበት ራሳቸውን የመግለጽ ንግግር ያደርጋሉ፤ ግጥም ይጽፋሉ፤ መጨረሻ የተሻለው ተመርጦ እንዲተርኩት ይደረጋል። ይህ ዋና አላማው በሁሉም ሰው ውስጥ አልተጻፈም እንጂ ሊተርከው የሚችል ትልቅ ድርሰት እንዳለ ለማሳየት ነው። የሚያወጣበት መንገድ አጥቶ እንጂ አቅም እንዳለው ማሳየት፣ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን እንዲያወጡ ማበረታታት ነው ዋና ዓላማው” በማለት ታብራራለች። እናም ጥበብ በአደባባይ ፋይዳው በአቅምና በአመለካክት ምክንያት ዕድሉን ያላገኙ ሰዎች የሚሰጠው ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች። “ባለፈው ዓመት ከዶክተሮች እስከ ጎዳና ልጆች እኔጋ መጥተው ተሳትፈዋል” የምትለው አስቴር በ‘ጥበብ በአደባባይ’ አላፊ አግዳሚ እግረኛ ሁሉ ጥበብ ይጠራዋል ባይ ናት። ሰዎችን እንዲህ ለጥበብ ማበረታታት በጎተ አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን በመንግስት ባለድርሻ ተቋማትም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር እንደሆነም ትናገራለች። የአክሽን ሚዲያና ኮሚኒኬሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ የፊልም ባለሙያው ሔኖክ መሐሪ በርካታ ተማሪዎች ከጥበብ ይልቅ ወደ ሳይንስ እንደሚያዘነብሉ ይገልጻል። እርሱም በኮምፒዩተር ሳይንስ መማሩንና በሂደት የጥበብ መክሊቱን ማግኘቱን ገልጾ፤ “ጥሩ ከያኒ የሚሆነውን ሰው መሀንዲስ ብታደርገው ውጤታማ አይሆንም፤ ስለዚህ ሁሉም ሰው ጥበብን ማወቅ አለበት” ይላል። በፊልም ጥበብ ኢንዱስትሪያችን ችግሮች መካከል (በቂ ማሰልጠኛ ተቋም ባለመኖሩ) የሙያዊ ዕውቀት ክህሎት ችግር ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራል። “ፊልም ማለት ምንድነው፣ እንዴት ይሰራል፣ መረጃዎችን የሚፈልጉ ልጆች መጥተው በተግባር መሳሪያዎችን አቅርበንላቸው ከዚሁ እያየናቸው የራሳቸው አጫጭር ፊልሞች ሰርተው እስቲ እንዴት ነው የሚለውን ነገር ያውቃሉ፤ አወደዋለሁ አልወደውም የሚለውን እንዲያውቁ ነው” በማለት ጥበብ በአደባባይ ፕሮግራም በፊልም ጥበብ ዘርፍ ስላለው ፋይዳ ይተርካል። ሄኖክ አክሎም “ኢትዮጵያ በመልካ ምድር፣ በአየር፣ በባህልም፣ በብዝኃንነትም የታደለች ናት፤ ይህን መሸጥ ይኖርብናል። እኛ ግን ይህ ዕድል ኖሮን አልተጠቀምንበትም። የኛን አገር በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ለርሀብና ድህነት ተምሳሌት ተደርጋ የነበረ አንድ ጊዜ ‘ቢቢሲ’ ላይ በታየች ምስል ነው አይደለ? እኛ ደግሞ ያንን ተጠቅመን አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንችላለን፣ ቱሪዝምን ማሳደግ ሌላውንም ነገር” ይላል። እናም ዘርፉን ፊልም የሚያደገው ሁልጊዜ መድረክ ላይ የምናያቸውን ብቻ ሳይሆን ወጣቶችን ማፍራትና ማሰልጠን ሲቻል እንደሆነ ገልጾ፤ ፊልም ማለት ብዙ ጥበብ ተደማምሮ የሚመጣ እንጂ ዝም ብሎ ካሜራ አንስቶ መቅረጽ እንዳልሆነ፤ በዛ ውስጥ ብዙ ሙያዎች እንዳሉ ለማሳየት እንደሚያስችል ያብራራል። እንዲህ አይነት ፕሮግራሞችም በሌሎች ተቋማትም (እንደ ፋሽን ሳይሆን) ቀጣይነት ኑሯቸው ቢሰሩ ለሙያው ትልቅ አበርክቶት እንዳለው ነው የሚገልጸው። ከተለያዩ ሱስ ቦታዎች ይልቅ እየተዝናኑ ጥበብን የሚቀስሙባቸው ዝግጅቶች ሊኖሩ ይገባል ባይ ነው። ተማሪ ያስሚን አብዱ ደግሞ በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ፣ የግንባታና ከተማ ልማት ተቋም የ5ኛ ዓመት ተማሪ ናት። “ጓዳና ጎዳና” በሚል ስለ ኪነ ህንጻ መሰረታዊ መርሆች፣ በቀላል ንድፍ፣ የናሙና ስራ ልምምዶች ላይ ያተኮረ የኪነ ህንጻ (አርክቴክቸር) ጥበብ ላይ ያተኮረ ዝግጅት ከባልደረቦቿ ጋር ይዛ ትሳተፋለች። በተለይ ለእነ ያስሚን ቡድን በዘንድሮው የጥበብ በአደባባይ ዝግጅት የቀረቡ ተንቀሳቃሽ ሱቆችን በመፍጠር የፈጠራ ችሎታቸውን ለማሳየት አጋጣሚውን ፈጥሮላቸዋል። ባላደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ስለ “አርክቴክቸር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቱ አንጻር ብዙ ትኩረት አይሰጠውም። እና ይህን ለማምጣት የሰው ግንዛቤ መዳበር አለበት። አዳዲስ ከተሞች ሲስፋፉ ከሌሎች የህንጻ ዲዛይንና ፕላን ይኮርጃሉ። ስለዚህ የራሳችን ጥበብና ማንነት ይዘን እንድንወጣ ለማድረግ ማኅበረሰባዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው” በማለት የጥበብ በአደባባይን አይነት መድረኮች ጠቀሜታ ታብራራለች።እናም እንደ ባለፈው ዓመት ስለ ኪነ ህንጻ ለማስተዋወቅ መዘጋጀታቸውን ትገልጻለች። ይህም ኪነ ህንጻ የከተማ ዲዛይን መሰረታዊ መርሆችን በመስጠት የፈጠራ ችሎታን እንደሚያነቃቃም ገልጻለች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ'አለ' የስነ ጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት ወጣቷ መምህርት ራህዋ ገብረሊባኖስ በፕሮግራሙ መጀመር መደሰቷን ትናገራለች። ስዕል በስቱዲዮ ወይም በጠባብ ዓውደ ርዕይ ብቻ ነው የሚንጸባረቀው። "ጥበብ በአደባባይ ግን ብዙ ህዝብ ስላለ ለአርቲስቱ ትልቅ ዕውቅናን ይፈጥርለታል" ትላለች። “ኢትዮጰያና የስዕል ጥበብ የተቆራኙ ናቸው፤ የረጅም ዓመት ግንኙነት አላቸው። ፊደላት ባልነበሩበት ዘመን በዋሻ ላይ ስዕሎች ሀሳባቸውን ገልጸዋል። ከቤተ ክርስቲያን ብትጀምር፣ የሰው የኑሮ ዘይቤ የምንለብሰው ልብስ ስዕል ነው፤ ግን እስካሁንም በሰዓሊና በማህበረሰቡ መካካለ ክፍተት አለ። በርግጥ እየኖረው ነው፤ ለምን ግምት እንዳልሰጠው ግን እንጃ” ትላለች ለስዕል ጥበብ ያለውን ማህበረሰባዊ እይታ። “ጥበብ ከሌለ አገር ታድጋለች ማለት ሕልም ይመስለኛል” የምትለው መምህሯ፤ ሰው ለስዕል ያለው አረዳድና ምልከታ እንዲያድግ እንዲህ አይነት ዕድሎች መልካም እንደሆኑ ነው የገለጸችው። በዚህ መድረክም ተሳታፊዎች ራሳቸውን እንዲስሉ ይደረጋል። ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲሳሳሉ ይደረጋል። እነዚህ ምስለሰቦች (ፖርትሬትስ) እንደ ሌሎች የተሳታፊዎች ጥበባዊ ሰራዎች ሁሉ በጊዜያዊ መካነ ጥበባትና በጎተ ኢንቲትዩት በፌስቲቫሉ መዝጊያ ይቀርባሉ። እናም በፌስቲቫሉ ሁሉም ሰው የፈጠራ ችሎታውን ይፈልጋል፤ ዝነኛ አርቲስቶችን ይተዋወቃል።