በመጪው ክረምት 600 ሺህ ዜጎችን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ እየተሰራ ነው

ባህር ዳር ኢዜአ ግንቦት 01/2012  በአማራ ክልል በመጪው የክረምት ወራት ሊከሰት ከሚችል ጎርፍ 600 ሺህ ዜጎችን ከአደጋው ለመጠበቅ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የአደጋ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በቅርቡ በተካሔደው ጥናት በመጪው ክረምት 600 ሺህ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉና በንብረት ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።

አደጋው ሊደርስ የሚችለው ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ በምስራቅና ምዕራብ አማራ ባሉ ስድስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 20 ወረዳዎች እንደሆነም አመልክተዋል።

ጉዳት ሊደርስባቸው ከሚችሉ ዞኖች መካከል የሰሜን ሸዋ ፣ኦሮሞ ብሄረሰብ ፣ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር አስተዳደር ዞኖች ይገኙበታል።

ሊደርስ ይችላል ተብሎ በጥናት የተለየውን የጎርፍ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ  50 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅትም ለጎርፍ መነሻ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ግንባታ፣ የእርከንና የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን የመጥረግና አዲስ የመገንባት ስራ እየተከነናወነ ነው።

በተለይ በደቡብ ጎንደር ዞን የርብና ጉመራ ወንዞች በደራ፣ ፎገራና ሊሞ ከምከም ወረዳዎች አካባቢ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት  ከግምት ያስገባ  ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ገልፀዋል።

በጣና ዙሪያ የጎርፍ አደጋው የከፋ ሊሆን ከቻለም ተፈናቃዮች የሚያርፉበት የድንኳን መጠለያዎችና ሌሎች ተቋማት የተዘጋጁ ሲሆን አራት የመጓጓዥ ጀልባዎችም ተዘጋጅተዋል።

ለተፈናቃዮች የሚሆን ምግብም ሆነ መጠለያዎችን ቀድሞ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ  ህብረተሰቡ በክረምቱ ወቅት ሊከሰት ከሚችል ድንገተኛ ጎርፍ እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ አቶ  ስዩም አስማረ በበኩላቸው  በዞኑ በተለይም የሊቦ ከምከም ወረዳ ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት የተጋለጠ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በርብ ወንዝ ዳርቻም ሦሰት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጎርፍ መቀልበሻና መውራጃ ቦይ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በጉዳቱ ሊፈናቀሉ ለሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያዊ መጠለያ የሚሆኑ ሁለት ተገጣጣሚ ድንኳኖች ተዘጋጅተዋል።

ምግብና ሌሎች ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶችን የማዘጋጀት ስራም እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም