የኢድ አል-ፈጥር በዓል እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ አል-ፈጥር በዓል እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ) ኢሺህ 441ኛው የኢድ አል-አፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው።
በዓሉ ወትሮ እንደሚከበረው የእምነቱ ተከታዮች በአንድ ስፍራ ተሰባስበው ሶላት እንደማይከናወን መመሪያ መሰጠቱን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስ መናገራቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ዛሬ በታላቁ አኑዋር መስጊድ በቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እድሪስ ምርቃት የተጀመረው የሶላት ሥነ-ስርዓት በቀጥታ በቴሌቪዥን ተላልፏል።
የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም ሼህ ጣሃ መሃመድ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያሳልፍ እንደወትሮው ለተቸገሩ ዘካ በመስጠትና በጋራ ሊሆን ይገባል።
"የእምነቱ ተከታዮች ኮሮናን ለመከላከል ሲባል በአንድነት ተሰባስቦ መስገድ እንደማይቻል የተላለፈውን መመሪያ አክብረዋል" ያሉት ኢማሙ ሕዝበ ሙስሊሙ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክር ስንሰጥ ቆይተናል ብለዋል።
የበዓሉ ደስታ ለሁሉም እንዲሆን ጎረቤቶችን መጠየቅና ማገዝን የእምነቱ አስተምህሮ እንደሚያዝ ጠቅሰው "በፈጣሪ ዘንድ የሚቆጠረው ለተራበና ለሌላው ስናስብ ነው" ሲሉ አክለዋል።
መንግሥት አበረታች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ሼህ ጣሃ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ 'ምስጋና ይገባቸዋል' ነው ያሉት።