በአማራ ክልል 2ሺህ 900 ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም ቀይ ሽንኩርት ማልማት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 2ሺህ 900 ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም ቀይ ሽንኩርት ማልማት ተጀመረ

ባህር ዳር /ኢዜአ/ ግንቦት 20/2012 በአማራ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ በክረምት ወቅት 2 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ ቀይ ሽንኩርት የማልማት ስራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ ።
የቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጥቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድም ለኢዜአ እንደገለጹት በሃምሌና ነሐሴ ወራት በተደጋጋሚ ከፍተኛ የቀይ የሽንኩርት እጥረት ያጋጥማል።
በክልሉ በበጋ ወራት በመስኖ የሚለማው ሽንኩርት የመቆየት እድሉ እስከ ሰኔ ወር ብቻ በመሆኑ የክረምት የሽንኩርት አቅርቦት ችግር ስር የሰደደ ሆኖ መቆየቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።
በገበያ ላይ የሚፈጠረውን የሽንኩረት እጥረት ለመሸፈንም በየዓመቱ እስከ 600 ሺህ ኩንታል ሽንኩርት ከሱዳን ወደ ክልሉ ሲገባ ነበር ብለዋል ።
የችግሩ አሳሳቢነት እየጎላ በመምጣቱና ህብረተሰቡ ለከፋ የዋጋ ጫና እየተዳረገ በመምጣቱ በዚህ የክረምት ወቅት የዝናብ ውሃን በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የአመራረት ዘዴ በመከተል ወደ ስራ ተገብቷል።
በክልሉ ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ምስራቅ ጎጃምና ሰሜን ሽዋ ዞኖች ለሽንኩርት ምርት አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት 2 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በሽንኩርት ዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።
"ቦምቤሬድ" የተሰኘ የቀይ ሽንኩርት ዝርያ ከግንቦት ወር መግቢያ ጅምሮ የለማ መሆኑን የገለጹት አቶ ይበልጣል እስከ ሰኔ ወር መጨረሻም ተመርቶ ለገበያ ይቀርባል ብለዋል ።
የክረምት የሽንኩርት ልማት የአቅርቦት እጥረት ከመቅረፍ በተጨማሪ ህዝቡ ለአንድ ኪሎ ግራም 35 ብርና ከዚያ በላይ ሲያወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በዚሁ የሽንኩርት ልማት ስራ በቂ ስልጠና የወሰዱና ቀደም ሲል የካበተ ልምድ የነበራቸውን 8 ሺህ 527 አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው ።
ኩታ ገጠም የቀይ ሽንኩርት አመራረት ስልቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የገለጹት ዳይሬክተሩ ከክልሉ ፍጆታ ባለፈ ለሌሎች ክልሎች በማቅረብ እንደ ሀገር ከውጪ የሚገባውን ምርት ለመተካት በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል ።
በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጌታሁን ሞላ በሰጡት አስተያየት አንድ ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርት መዝራታቸውን ተናግረዋል ።
ካለሙት መሬትም 400 ኩንታል ሽንኩርት እንደሚጠብቁ ገልጸው ለማምረት የሚያስችል ሙያዊ ስልጠና ማግኘታቸውን አስረድተዋል ።
ለዘር የሚሆን የሽንኩርት ዝርያ ከማቅረብ ጀምሮ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያስረዱት አርሶ አደር ጌታሁን ከወዲሁ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል።
ሌላኛው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ምትኩ ሞላ በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት ሽንኩርት ግንቦት መግቢያ ላይ ከሌሎች አምራች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ማልማታቸውነ ተናግረዋል።
የኩታ ገጠም አስተራረስ ስልቱ ሽንኩርቱን ለመንከባከብም ሆነ ለጥበቃ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል።
በክልሉ ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት 90 ሺህ ሄክታር መሬት በአዲስ ወደ ሰብል ልማት እንዲገባ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱ መገለፁ ይታወሳል።