የሰንበት ገበያ ማእከላት መቋቋም የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለማቃለል አስችሏል - በአርባ ምንጭ ከተማ ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
የሰንበት ገበያ ማእከላት መቋቋም የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለማቃለል አስችሏል - በአርባ ምንጭ ከተማ ሸማቾች

አርባምንጭ ሚያዚያ 05/2015 (ኢዜአ) የሰንበት ገበያ ማዕከላት መቋቋማቸው የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለማቃለል አስችላል ሲሉ የአርባምንጭ ከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
ገበያን ለማረጋጋት የሰንበት ገበያ ማእከላትን በማቋቋምና ዩኒየኖችና ህብረት ሥራ ማህበራትን በማስተባበር ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ ማድረጉን የጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ነፃነት መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት ገበያን ለማረጋጋት ከተቋቋሙ የሰንበት ገበያ ማዕከላት ለበአል የሚሆኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ችለዋል።
በመደበኛ ገበያ በ100 ብር የሚሸጥ አንድ ኪሎ ስኳር በ75 ብር እንዲሁም በ150 ብር የሚሸጥ አንድ ሊትር ዘይት በ140 ብር መግዛታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
"ገበያን ለማረጋጋት የተቋቋሙ የሰንበት ገበያ ማዕከላት ለበዓል ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
ወይዘሮ አበበች ባቸው በበኩላቸው የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ከሰንበት ገበያ የተለያዩ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ መሸመት እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የሰንበት ገበያ መቋቋም የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ለማቃለል አስተዋጾ አድርጓል።
ህብረተሰቡ ያለአግባብ በሚደረግ የዋጋ ጭማሪ እንዳይጎዳ ገበያ የማረጋጋት ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
ገበያን ለማረጋጋት በአርባምንጭ፣ በገረሴ፣ በካንባ፣ በምዕራብ አባያና ሰላም በር ከተሞች የሰንበት ገበያ ማዕከላት መቋቋማቸውን የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም ዛፉ ናቸው።
በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ ዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራትን በማስተባበር በሰንበት ገበያው የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች በስፋት እንዲያቀርቡ መድረጉን ገልጸዋል።
በሰንበት ገበያ ማእከላት ከፋብሪካ ምርቶች ስኳር፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እንዲሁም ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጤፍ፣ ዶሮ፣ ዕንቁላልና ሌሎች የግብርና ምርቶች በስፋትና ከዋናው ገበያ በተሻለ ዋጋ መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
የምርት እጥረትና ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ገበያ አረጋጊ ግብረ ሃይል በማቋቋም በሁሉም ማዕከላት ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትንሳኤና የኢድ አልፈጥር በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሰንበት ገበያዎች ሳምንቱን ሙሉ የሚሰሩ መሆኑን ሀላፊዋ አስታውቀዋል።
ዶታ የሰብል አምራች ገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን" የምርት ስርጭት ሠራተኛ አቶ አሰማኝ ጌታቸው በበኩላቸው ዩኒየኑ የግብርና ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ችግር ለማርገብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"የትንሳኤና ኢድ አልፈጥር በዓላትን ምክንያት በማድረግ በቆሎና ዘይት በተመጣጣሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረብን ነው" ብለዋል።
"በመደበኛ ገበያ በኪሎ 40 ብር የሚሸጥ አንድ ኪሎ በቆሎ በዩንየኑ በኩል በ33 ብር እንድሁም ዘይት ሊትር በ20 ብር ቅናሽ እየሸጥን ነው" ሲሉም ጠቅሰዋል።
ጽናት የዶሮ እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ ወይዘሮ ታሪኳ ሲሳይ በበኩላቸው ማህበሩ ከመደበኛው ገበያ በ5 ብር የቅናሽ ልዩነት ዕንቁላል በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል ።