የሴቶችና ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የዲጂታል ምህዳሩን ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የዲጂታል ምህዳሩን ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ)፦የሴቶችና ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የዲጂታል ምህዳሩን ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የወጣት ሴቶች ዓለም አቀፍ የአይ ሲ ቲ ቀን “ዲጂታል ክህሎት ለሕይወት” በሚል መሪ ኃሳብ በተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተከብሯል።
በተ.መ.ድ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ክፍል ባለሙያ ባህታ ማሞ መድረኩ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ በትምህርትና በተለያዩ ሥራዎች ላይ የሚገኙ ወጣት ሴቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፈችው ተማሪ ገብርኤላ ይገዙ እንደዚህ አይነት መድረኮች የልምድ ልውውጦችን ለማካሄድና ትስስር ለመፍጠር ይጠቅማል ብላለች።
እንዲያም ሆኖ ሴቶችና ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚኖራቸውን ተጠቃሚነት ይበልጥ ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ አመልክታለች።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ሁነቶች ሴቶች በቴክኖሎጂና ዲጂታል ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ያግዛል ብለዋል።
ሁነቶችን ከማክበር ባለፈ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ሰፊ አቅምና ተደራሽነት ከግምት ያስገባ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ከትምህርት ቤት ጀምሮ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያም አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፉ ትኩረት በመስጠት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ወጣቶችና ሴቶች ውጤታማ የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሥርዓተ-ትምህርት በመቅረጽ ወደ ሥራ ተገብቷል ሲሉም ገልጸዋል።
ሥርዓተ-ትምህርቱ በዩኒቨርስቲና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመው ከትምህርት ውጪ ያሉትን ደግሞ በሥልጠናዎች በማብቃት በዘርፉ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።