የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ግብርናን ለማዘመን

ሚዛን አማን ሰኔ 08/2015 (ኢዜአ) በክልሉ ያለውን የግብርና ልማት ለማሳካት ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው "የዘመነ ግብርና ለኢትዮጵያ ብልጽግና!" በሚል መሪ ሐሳብ  የሜካናይዜሽን ሥራ ላይ ያተኮረ ክልላዊ የውይይት መድረክ ከዞንና ወረዳ የዘርፉ አመራር ጋር በሚዛን አማን እያካሄደ ነው።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ የጽህፈት ቤት ኃላፊና የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ አቶ ዮሐንስ መላኩ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በግብርና ሥራ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን መሻገር የሚቻለው በቴክኖሎጂ በመደገፍ ነው። 

በክልሉ ሰፊ  ማሳና አምራች ኃይል ቢኖርም፤ በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ስለሚሰራ ከዘርፉ ተገቢው ምርትና ምርታማነት እንዳይገኝ እያደረገ ነው ብለዋል።

ይህን የግብርና ዘርፍ ተግዳሮት ለመሻገርም የክልሉ መንግስት በቴክኖሎጂ ታግዞ ለማምረት 

ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ከ37 በላይ ትራክተሮችን በገጠር ለተደራጁ ወጣቶች ማስረከቡን ገልጸዋል።

የቢሮው  የግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ አሥራት አሰፋ በበኩላቸው ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ግብርናን ማዘመን ብቸኛ አማራጭ ነው ብለዋል።

የግብርና ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሪያና የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚመረትበት ሰፊ የኢኮኖሚ መሠረት እንደሆነም አስረድተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም