በአማራ ክልል የተገልጋዩን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማርካት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተገልጋዩን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማርካት እየተሰራ ነው

ባህርዳር ሰኔ 9/2015 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል ስቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን የመንግሥት ሰራተኛኞችን አቅም በመገንባት የተገልጋዩን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማርካት እየተሰራ መሆኑን አስወቀ።
ከክልሉ ሶስት ዞኖችና ከሶስት ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ከ900 ለሚበልጡ የቡድን መሪዎች ለአምስት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በባህርዳር ከተማ ዛሬ መስጠት ተጀምሯል።
ስልጠናው እየተሰጠ ያለው ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ከማዕከላዊና ከደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ከባህርዳር፣ ከደብረተቦርና ከጎንደር ከተሞች አስተዳደሮች ለተውጣጡ የቡድን መሪዎች እንደሆነም ተገልጿል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እመቤት ምትኩ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት አሁን ላይ ህብረተሰቡን ለምሬት እየዳረጉ የሚገኙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ይስተዋላሉ።
በተለይ እንደመሬት ማኔጅመንት፣ ንግድ፣ ገቢዎችና ሌሎች ተቋማት አንዳንድ ባለሙያዎች በስነምግባር ጉድለት ህብረተሰቡን ላላስፈላጊ እንግልት እየዳረጉት እንደሆነም ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማረም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን በመስጠት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ እርካታ ለመፍጠር ኮሚሽኑ ችግሮችን ለይቶ ወደስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ወር ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከክልሉ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከየተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ 351 ዳይሬክተሮች ስልጠና ሰጥቷል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር እመቤት የስልጠናው ዓለማ የአገልግሎት አሰጣጡን የግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ባሰፈነ መልኩ ተደራሽ በማድረግ የመልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደርና የአረንጓዴ ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ እናንዬ አየልኝ እንዳሉት ስልጠናው የስራ ተነሳሽነትና የአገልጋይነት መንፈስ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው።
ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የሚፈልገውን አገልግሎት በአግባቡና በወቅቱ መስጠት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
ከስልጠናው በማያገኙት ተጨማሪ እወቀት የሚያስተባብሯቸው ባለሙያዎች ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል
የደቡብ ጎንደር ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የስቪል ምህንድስና ቡድን መሪ አቶ ሰሎሞን ባዘዘው በበኩላቸው ስልጠና በቅንነትና በታማኝነ ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በርካታ ባለጉዳዮች እየተጉላሉ ያሉት አንዳንድ የእጅ መንሻ በሚፈልጉ ባለሙያዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ታግለው ለማስተካከል ስልጠናው ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል።
በአማራ ክልል ከ458 ሺህ የሚበልጡ የመንግስት ሰራተኞች እንዳሉ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።