በኢትዮጵያ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው - የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው - የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2015 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑን የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝምን አንዱ አንቀሳቃሽ በማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች፡፡
በገበታ ለሸገርና በገበታ ለአገር መርሃ ግብር እንደ አንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርክ እንዲሁም ወንጪ፣ ጎርጎራና ኮይሻ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት አብዛኞቹ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንትና የዓለም ትታይ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ዕንቁ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ብዝሃ ሃብት መገኛ፤ የተፈጥሮ፣ የባህልና ታሪክ ባለቤት ጥንታዊት ሀገር ነች፡፡
መንግስት ለቱሪዝም ትኩረት በመስጠት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባቱ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኤልገል ሆቴልና ስፓ ስራ አስኪያጅ አለማየሁ ፍቅረማርያም በበኩላቸው የቱሪስት መዳረሻዎች መስፋፋት የቱሪስት ፍሰቱን በማሳለጥ የጎብኚውን የቆይታ ጊዜ እያራዘመ ነው፡፡
በቱሪዝም ዘርፉ ለ28 ዓመታት እንዳገለገሉ የሚገልጹት ዕንቁ ሙሉጌታ፤ አስጎብኚዎች በቱሪዝም ዓውደ ርዕዮችና አብረዋቸው ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘርፉን የሚያስተዋውቁበት የረጅም ጊዜ አሰራር ልምድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
የቲ.ኤች ቦን ሮያል ሆቴል የሰው ኃብት አስተዳደር ኤደን ብዙነህ በበኩላቸው እንግዶች የቱሪስት መዳረሻዎችን በተመለከተ እውቅና እንዲኖራቸው የማስተዋወቅ ሥራ እናከናውናለን ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ታሪኩ ሀይሉ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የሚሰሩ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ በግለሰብም ሆነ በማህበር ደረጃ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤንዲ አሰፋ ናቸው።