መከላከያ ሠራዊት ሃገርን በጀግንነት የሚያስጠራና ሉአላዊነቷን የሚያስጠብቅ ተቋም በመሆኑ እናጠናክረዋለን

ሀዋሳ ፤ጥቅምት 15/2016 (ኢዜአ)፦ ክልሉ የመከላከያ ሠራዊት ሃገርን በጀግንነት የሚያስጠራና ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቅ ተቋም በመሆኑ እንዲጠናከር ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አስታወቁ፡፡

"በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት" በሚል መሪ ቃል 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ዛሬ  በሀዋሳ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በጀግንነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነትና ባስመዘገቡት ጀግንነት  ነው፡፡

መከላከያ ሠራዊት ሃገርን በጀግንነት ከሚያስጠሩት ግዙፍ ተቋማት ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው፣ተቋሙ ኢትዮጵያን የሚመስል ሆኖ በመገንባቱ  ለሕዝብ የሚተማመንበት አቅም ሆኗል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት መከላከያ ሠራዊቱን ለማጠናከር በሚደረገው እንቅስቃሴ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግም ኃላፊው  አረጋግጠዋል፡፡

በሃገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ ተቋሙን በአዲስ መልክ ለማደራጀት የተደረገው ጥረትም ኅብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ ተቋም ለመገንባት እንዳስቻለም አመልክተዋል፡፡  

የክልሉ መንግሥት ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ ወጣቶችን በመመልመልም ሆነ ሃገር በተፈተነች ጊዜ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት አቶ አለማየሁ፣ አሁንም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡


 

የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው የሃገር መከላከያ ሠራዊት ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት የሃገርን ሉዓላዊነት ያስከበረ ባለታሪክ በመሆኑ ትልቅ ክብርና ድጋፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሠራዊቱ መስዋዕትነትና የህዝብ አንድነት ሃገር በተለያዩ ጊዜያት የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድል እንድትወጣ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡


 

የደቡብ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ኮሎኔል ወንድወሰን አስፋው በበኩላቸው የሠራዊት ቀን መከበሩ የአባቶችን ታሪክ ለማስታወስና የሠራዊቱን ጀግንነት ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

ሠራዊቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚገጥሙትን ፈተናዎችን በማለፍ የሃገር ሉአላዊነትን ለማስከበርና ጀግንነቷን ለማስጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ ከህዝቡ የወጣ፣ በህዝቡ ድጋፍ የሚንቀሳቀስና ሃገርን የሚያስቀጥል መሆኑን የገለጹት ኮሎኔል ወንድወሰን፣ ህዝቡና መከላከያ ሠራዊቱ አሁንም ለሃገር አንድነት በጋራ መቆማቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

''ሠራዊቱ ለሃገር ክብርና ሉአላዊነት መስዋዕትነት የሚከፍል በመሆኑ ቀኑን ማሰብ ሃገርን ማክበር ነው'' ያሉት ደግሞ በበዓሉ የታደሙት የቀድሞ የሠራዊት አባል አስጨናቂ ስንታየሁ ናቸው፡፡


 

የአሁኑ ትውልድም መከላከያ ሠራዊቱ ለሃገር ፍቅር እየከፈለ ካለው መስዋዕትነት በመማር ለሠራዊቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

በበዓሉ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ዕዝ ሠራዊት አባላትና የጦር መኮንኖች፣ የፌዴራልና የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ አባላት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአካበቢው ነዋሪዎችም በበዓሉ ታድመዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም