የአደዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም የግንባታ ሒደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአደዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም የግንባታ ሒደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2016(ኢዜአ)፦የአደዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ፕሮጀክቱን ተዘዋውረው የተመለከቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አንጋፋ የታሪክ ምሁራን እና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ምሁራኑ የመላው አፍሪካዊያን ኩራት የሆነው የዓድዋ ሙዚየም ግንባታ ታሪካዊ እውነቱን የሚተርኩና የሚዘክሩ ትዕምርቶች በተካተቱበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ሙዚየሙ በከተማዋ ውስጥ ከተገነቡ እና በመገንባት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ግዙፉ ሲሆን 11 ብሎኮችን የያዘና ሰፊ ቦታ ላይ እየተገነባ ያለ በውስጡም የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የአድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ እና የአንድነት ማዕከል ያካተተ ነው።
በተጨማሪም የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጀግኖችን ጉዞ የሚያሳይ ሙዚየም ፣ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ300 እስከ 4000 ሰው ድረስ የሚይዙ የተለያዩ አዳራሾች የሚገኙበትም ነው።