ሃይል ቆጣቢ የኢነርጂ አማራጮችን ለማህበረሰቡ ለማዳረስ እየተሰራ ነው

ደብረ ብርሃን፤ታህሳስ 13 /2016 (ኢዜአ) ፡- ለገጠሩ ማህበረሰብ ሃይል ቆጣቢ  የኢነርጂ  አማራጮችን ተደራሽ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ  ድጋፍ የማከፋፈል ስነ ስርዓት ዛሬ በባሶና ወራና ወረዳ ተካሄዷል።

በሚኒስቴሩ የኢነርጅ ሀብት ልማት ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሌብ ታደሰ በወቅቱ እንዳሉት፤ በአባይ ተፋሰስ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የውሃ መሰረተ ልማትና የህብረተሰቡን ያሳተፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም  ስራዎች  እየተሰሩ ነው።


 

በዚህም የገጠር አማራጭ የሀይል አቅርቦትን ለማሻሻል ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በተገኘ  ድጋፍ 1 ሺህ 521 ማገዶ ቆጣቢና የአየር ብክለትን የሚከላከሉ ቴክኖሎጂዎችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በሰሜን ሸዋ ዞን  ከባሶና ወራና ወረዳ ለተውጣጡ 248 ሴቶች ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች የሚሰራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም  ሃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ በደን ሃብቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመከላከል፣የእናቶችና የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ውሃና ኢነርጅ መምሪያ የኢነርጅ ዘርፍ የሀይል አማራጭ ቡድን መሪ አቶ ክብሩይስፋ ዲበኩሉ በበኩላቸው፤ በተያዘው ዓመት የተሻሻሉ የሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪ በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር በአባይ ተፋሰስ ስር ለሚገኙ አምስት ወረዳዎች 500 የእንጀራ ምጣድ፣ 248  ለቡናና ለወጥ ዝግጅት የሚውሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፍ የአካባቢውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ የዞኑ  ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ የሮም ነሽ ጋሻውጠና ናቸው።  

ይህም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከደለል ለመጠበቅ በአፈርና ውሃ ጥበቃ በስነ ህይወት ዘዴ ከምናደርገው ድጋፍ ባሻገር የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ከተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ዓይናለም በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ ድጋፉ ድካምና በጭስ ከመታፈን ችግር በማላቀቅ ለምግብ ማብሰያ የሚውል ከሰል ፍጆታን በእጅጉ እንደሚቀንስ ከተደረገላቸው ገለጻ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ  ስርጭት ስነ ስርዓቱ ከባሶና ወራና ወረዳ የተውጣጡ አርሶ አደሮችና በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም