የአፍሪካ እግር ኳስ ፈር ቀዳጇ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ዋንጫ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ እግር ኳስ ፈር ቀዳጇ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ዋንጫ

እንደ መነሻ
እ.አ.አ የካቲት 8 ቀን 1957 በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ከሚባሉ ቀናት ውስጥ አንዱ ነው።
በካርቱም ግራንድ ሆቴል ሱዳን፣ኢትዮጵያ፣ግብጽና ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራውን ተቋም ለመመስረት ምክክር ላይ ናቸው።
አህጉሪቷን የሚወክለው ኮንፌዴሬሽን ለማቋቋም መነሻ የሆነው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) እ.አ.አ በ1956 በፖርቹጋል ሊዝበን ባካሄደው ዓመታዊ ኮንግረስ ላይ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች ከሌሎች አህጉራዊ የእግር ኳስ ማህበራት ጋር ያደረጓቸው መደበኛ ምክክሮች ናቸው።
በካርቱም የተሰበሰቡት አራት አገራት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በይፋ መሰረቱ። ግብጻዊውን አብደል አዚዝ አብደላ ሳሌምን በሙሉ ድምጽ የካፍ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት አድርገው መረጡ።
ካፍን ያቋቋሙት አገራት እ.አ.አ በ1957 የአፍሪካ ዋንጫ በሱዳን እንዲካሄድ ወሰኑ።
የመጀመሪያውን የካፍ መተዳደሪያና የውድድር ደንቦች ያዘጋጁት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው።
የኢትዮጵያ የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና የፎርፌ ውጤት
የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ ከየካቲት 10 እስከ 16 1957 በሱዳን ካርቱም ተካሄዷል። በውድድሩ ላይ ሱዳን፣ኢትዮጵያና ግብጽ ተሳታፊ ነበሩ።
አስቀድሞ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ትሳተፋለች ተብሎ የነበረው ደቡብ አፍሪካ ከአገሪቷ በነበረው የአፓርታይድ የዘር መድሎ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
ደቡብ አፍሪካ ከውድድሩ ውጪ የሆነቸው በአፓርታይድ ሕግ ነጮች ሙሉ በሙሉ በነጭ ወይም በሙሉ የተገነባ ብሔራዊ ቡድን እንጂ መቀላቀል አንችልም በማለታቸው ምክንያት ነው።
በዚህም ምክንያት ከደቡብ አፍሪካ ጋራ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዋን ልታደርግ የነበረችው ኢትዮጵያ 2 ለ 0 በፎርፌ በማሸነፍ ለፍጻሜው አልፋለች።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ግብጽ ሱዳንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አለፈች።
እ.አ.አ የካቲት 16 1957 በካርቱም ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ግብጽ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ ታሪካዊውን የአፍሪካ ዋንጫ አነሳች።
አራቱንም ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመር ተጫዋቹ መሐመድ ዲያብ አል-አታር ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ አራት ግቦችን ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋችና በአምስት ግቦች የመጀመሪያው የውድድሩ ኮከብ ግቢ አግቢ በመሆን ድርብ ታሪክ ጽፏል።
ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች።
በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ምንም የማጣሪያ ውድድር አልተደረገም።
በመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ግብ ጠባቂ ሚካኤል ጊላ ተከላካዮች አየለ ተሰማ፣መኩሪያ ከበደ አስፋው፣አዳሙ ዓለሙ፣አዳል ተክለስላሴ አማካዮች ናስር በርሄና ሳሙኤል ዘውዴ አጥቂዎች አብርሃም ባይሩ፣አምደስላሴ ነጸረ፣አስፋው ብርሃኔና ከበደ መታፈሪያ ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫና እግር ኳስ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን በሱዳን አሀዱ ብላ ጀመረች።
የኢትዮጵያ ሁለተኛ ተሳትፎ
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1959 በግብጽ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ አድርጋለች። ሱዳን ሌላዋ በውድድሩ ላይ የተሳተፈች አገር ናት።
የውድድሩ ፎርማት በአገራቱ መካከል እርስ በእርስ በሚደረጉ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የሚያነሳበት ነበር።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በውድድሩ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች በግብጽ 4 ለ 0፤ በሱዳን 1 ለ 0 ተሸንፋለች።
በፍጻሜው ግብጽ ሱዳንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች።
ኢትዮጵያ ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችበት ታሪካዊ አጋጣሚ
ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተካሄደው በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እ.አ.አ በ1962 ነው።
የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሩ ቀደም ብለው ከተካሄዱት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ለየት የሚያደርገው አራት አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉበት ነው።
ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ በመሆኗ ሀገራችን በቀጥታ ለውድድሩ ስታልፍ ፤ በተመሳሳይ የግብፅ ቡድንም የ1959 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ስለነበር በቀጥታ ለ3ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ ዩጋንዳና ቱኒዚያ የማጣሪያ ጨዋታ አድርገው ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈዋል።
በሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ ውድድሩን ያስተናገደው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስታዲየም(የአሁኑ አዲስ አበባ ስታዲየም) ነበር።
ኢትዮጵያ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዋ ቱኒዚያን 4 ለ 2 አሸንፋለች።
አጥቂው ሉቺያኖ ቫሳሎ በ32ኛው በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ያስቆጠረችው የመጀመሪያ ግቧ ሆኖ ተመዝግቧል።
ቫሳሎ በ75ኛው ደቂቃ በጨዋታ ግብ አስቆጥሯል። አጥቂው መንግስቱ ወርቁ እና ግርማ ተክሌ ቀሪዎችን ግቦች ለኢትዮጵያ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ግብጽ ዩጋንዳን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜው ከኢትዮጵያ ጋር ደረሰች።
በፍጻሜው ጨዋታ አሊ መሐመድ ባዳዊ አብደል ፋታህ በ35ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት በግብ ግብጽን መሪ ማድረግ ችላ ነበር። ከእረፍት መልስ ግርማ ተክሌ በ74ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያን አቻ አድርጋለች።
በ75ኛው ደቂቃ አሊ መሐመድ ባዳዊ አብደል ፋታህ በድጋሚ ግብጽን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጠረ።
አጥቂው መንግስቱ ወርቁ በ84ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያን በድጋሚ አቻ አደረገ። ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ጨዋታው ወደ ጭማሬ ሰዓት አምርቷል።
በጭማሬ 30 ደቂቃው ኢታሎ ቫሳሎ በ101ኛው እና መንግስቱ ወርቁ በ118ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች ኢትዮጵያ 4 ለ 2 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉራዊውን ዋንጫ ከፍ አድርጋለች።
በፍጻሜው ጨዋታ ሁለት ግቦች ያስቆጠረው አጥቂው መንግስቱ ወርቁ በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨርሷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስት አገራት የተሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ
የኢትዮጵያ ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እ.አ.አ በ1963 በጋና አስተናጋጅነት በተካሄደው አራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው።
በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስት ብሔራዊ ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን በሁለት ምድብ እያንዳንዳቸው ሶስት አገራት ተደልድለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
የውድድሩ ፎርማት በየምድቡ አንደኛ ሆኖ የጨረሰ አገር ወደ ፍጻሜው እንዲሁም ሁለተኛ የወጡ አገራት ለደረጃው ያለፉበት ነበር።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጅ አገር ጋና ቱኒዚያ ጋር ተደልድላች።
በአክራ ስፖርት ስታዲየም ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ባደረገችው ጨዋታ 2 ለ 0 ተሸንፋለች።
በሁለተኛ ጨዋታዋ ኢትዮጵያ አጥቂው መንግስቱ ወርቁ ሁለት እንዲሁም ግርማ ተክሌና ግርማ ተስፋዬ ባስቆጠሯቸው አንድ አንድ ግቦች ቱኒዚያን 4 ለ 2 አሸንፋለች።
ኢትዮጵያ ከምድቡ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቋ ለደረጃ ጨዋታ የቀረበች ሲሆን በግብጽ 3 ለ 0 ተሸንፋለች።
በፍጻሜው ጋና ሱዳንን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አነሳች።
ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ የተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1965 በቱኒዚያ አስተናጋጅነት በተካሄደው አምስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ተሳትፋለች።
በውድድሩ ላይ ስድስት አገራት ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከቱኒዚያና ሴኔጋል ጋር ተደልድላለች። በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በቱኒዚያ 4 ለ 0 ተሸንፋለች።
ኢትዮጵያ በሁለተኛው የምድብ ጨዋታዋ በሴኔጋል 5 ለ 1 ተሸንፋለች። በጨዋታው ለኢትዮጵያ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሉቺያኖ ቫሳሎ በፍጹም ቅጣት ምት ነበር።
በፍጻሜው ጋና ቱኒዚያን 3 ለ 2 በማሸነፍ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ ማንሳት ችላለች።
ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ
እ.አ.አ 1968 የተካሄደውን ስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያዘጋጀችው ኢትዮጵያ ነበረች።
ውድድሩን ያስተናገደው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስታዲየም(የአሁኑ አዲስ አበባ ስታዲየም) ነበር።
በሻምፒዮናው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት አገራት ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከኮትዲቭዋር፣አልጄሪያና ዩጋንዳ ጋር የተደለደለች ሲሆን ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎቿን አሸንፋለች።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ ኢትዮጵያ ግርማ አስመሮም ተስፋይ በጨዋታና ሉቺያኖ ቫሳሎ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ግቦች ዩጋንዳን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ኢትዮጵያ በሁለተኛ ጨዋታዋ በኩረጽዮን ገብረሕይወት ባስቆጠራት ግብ ኮትዲቭዋርን 1 ለ 0 ረታለች።
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ አጥቂው መንግስቱ ወርቁና ሸዋንግዛው አጎናፍር በጨዋታ እንዲሁም ሉቺያኖ ቫሳሎ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ግቦች አልጄሪያን 3 ለ 1 በማሸነፍ ከምድቧ አንደኛ በመውጣት ለግማሽ ፍጻሜው አልፋለች።
ኢትዮጵያ በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታዋን ያደረገችው ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ነበር።
ራውል አልበርት ኪዱሙ ማንታንቱ በሶስተኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን መሪ አድርጎል። ሊኦን ሙንጋሙኒ በ16ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ የኮንጎን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርጓል።
ሉቺያኖ ቫሳሎ በ25ኛው ደቂያ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያን ወደ ጨዋታው እንድትመለስ አድርጓል።
መንግስቱ ወርቁ በ65ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ጨዋታው ወደ ጭማሪ 30 ደቂቃ አመራ።
በጭማሬ ሰዓቱ ሊኦን ሙንጋሙኒ በ100ኛው ደቂቃ ያስቆጠራትን ግብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን አሸናፊ በማድረግ ወደ ፍጻሜው እንድታልፍ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ለደረጃው ባደረገችው ጨዋታ ላውረን ፖኩ ባስቆጠራት ግብ 1 ለ 0 ተሸንፋ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው ውድድር አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግብ ያስተገደችበት ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ
ሱዳን እ.አ.አ 1970 ሱዳን ባዘጋጀችው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ለሰባተኛ ጊዜ በአህጉራዊው የውድድር መድረክ ተሳትፋለች።
በውድድሩ ላይ ስምንት አገራት ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከኮትዲቭዋር፣ካሜሮንና ሱዳን ጋር ተደልድላለች።
ኢትዮጵያ በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋ በሱዳን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተረታለች።
በሁለተኛው ጨዋታም በካሜሮን 3 ለ 2 የተሸነፈች ሲሆን መንግስቱ ወርቁ ለኢትዮጵያ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ በኮትዲቭዋር 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፋለች። መንግስቱ ወርቁ ለኢትዮጵያ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ላይ ያሳረፈ ተጫዋች ነበር።
በዚህ ጨዋታ አጥቂው ላውረን ፖኩ አምስት ግቦችን አስቆጥሯል።
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ በምድቡ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን በውድድሩ 12 ግቦችን ተቆጥረውባታል።
በፍጻሜው ሱዳን ጋናን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች።
ኢትዮጵያ ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ስምንተኛ ተሳትፎዋን ለማድረግ ስድስት ዓመት መጠበቅ ነበረባት።
እ.አ.አ በ1976 ራሷ ለሶስተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ በድጋሚ ወደ ውድድር ተሳትፎ ተመልሳለች።
በውድድሩ ላይ አሁንም የተሳተፉ አገራት ቁጥር ስምንት ነበር።
ኢትዮጵያ በውድድሩ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ዩጋንዳና ጊኒ ጋር ተደልድላለች።
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሰለሞን ሽፈራውና ተስፋዬ ስዩም ግቦች ዩጋንዳን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
በሁለተኛ ጨዋታዋ ኢትዮጵያን በጊኒ የ2 ለ 1 ሽንፈት አጋጥሟታል። ሰለሞን ሽፈራው ኢትዮጵያን ከሽንፈት ያልታደገችውን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። መሐመድ አሊ ለኢትዮጵያ ግቧን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአራት ነጥብ ከምድቧ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቋ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።
በፍጻሜው ሞሮኮ ጊኒን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ቻለች።
የኢትዮጵያ ዘጠነኛ ተሳትፎ በአህጉራዊው መድረክ
እ.አ.አ 1982 ኢትዮጵያ በሊቢያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለዘጠነኛ ጊዜ ተሳትፎዋን ማድረግ ቻለች።
በውድድሩ ላይ አሁንም ስምንት አገራት ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከአልጄሪያ፣ዛምቢያና ናይጄሪያ ጋር ተደልድላ ጨዋታዎቿን አድርጋለች።
በምድብ ጨዋታዎቹ በናይጄሪያ 3 ለ 0 እንዲሁም በዛምቢያ 1 ለ 0 የተሸነፈች ሲሆን ከአልጄሪያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።
ኢትዮጵያ በምድቧ አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
በፍጻሜው ጨዋታ ጋና ሊቢያን በመለያ ምት በማሸነፍ ለሶስተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካው ዋንጫ የተመለሰችበት ታሪካዊ ሁነት
ኢትዮጵያ ከ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ በአህጉራዊው የእግር ኳስ ውድድር መድረክ ለመሳተፍ ሶስት አስርት ዓመታታን መጠበቅ ግድ ሆኖባታል። በነዚህ 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 15 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ተካሄደዋል።
እ.አ.አ በ2013 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ ውድድሩ ዳግም ተመለሰች።
ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችበት መንገድ ልብ አንጠልጣይ ነበር።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2012 በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከሱዳን ጋር ባደረገችው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ በመጀመሪያ ዙር ኦምዱርማን ላይ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ተሸንፋለች።
ሱዳን ጨዋታውን ያሸነፈችው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት አጨቃጫቂ የፍጹም ቅጣት ምት በግቦች ነበር።
ጥቅምት 4 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ በስታዲየሙ ዙሪያ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ በርካታ ተመልካች ተሰልፎ ነበር።
ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም መጠናቀቁ በስታዲየሙ የተገኘውን ተመልካች ጭንቅ ውስጥ ከቶ ነበር። ጭንቀቱ በስታዲየሙ ላሉት ብቻ ሳይሆን በቴሌቪዥን መስኮት ለሚከታተሉት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻ እንቅስቃሴ ያደረጉት ዋልያዎቹ አዳነ ግርማ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ቻሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ አንድ ተጨማሪ ጎል ያስፈልጋታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ወሳኟን ሁለተኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳረፈ። ግቡ ሲቆጠር በስታዲየሙ ተመልካቾች ላይ የነበረው ስሜት በከፍተኛ ደስታ የተሟላ ሲሆን ስሜታቸውንብ በእንባ የገለጹም ነበሩ።
ጨዋታው በድምር ውጤት 5 ለ 5 ተጠናቆ ከሜዳ ውጪ ብዙ ባስቆጠረ በሚል ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ቻለች።
ከጨዋታው በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም፣በመስቀል አደባባይና በመዲናዋ የተለያዩ አውራ ጎዳናዎች፣መንደሮችና የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ክፍሎች የነበረው የደስታ ስሜትና ፈንጠዝያ የሚረሳ አልነበረም።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የደስታው ተቋዳሽ ነበሩ።
ኢትዮጵያን ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንድትመለስ ያደረጉት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ነበሩ።
ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 16 አገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ኢትዮጵያም በምድብ ሶስት ከቡርኪናፋሶ፣ናይጄሪያና ዛምቢያ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን አድርጋለች።
በመጀመሪያ ጨዋታዋ ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። አዳነ ግርማ በ65ኛው ደቂቃ ለኢትዮጵያ ግቡን አስቆጥሯል።
በሁለተኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ በቡርኪናፋሶ የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዳለች።
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ በናይጄሪያ 2 ለ 0 ተሸንፋለች።
ውጤቶቹን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛ ከምድቧ ሳታልፍ ቀርታለች።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብትመለስም በውድድሩ ላይ ያስመዘገበችው ውጤትና ያሳየችው ብቃት የእግር ኳስ ቤተሰቡን ያስደሰተ አልነበረም።
ይሁንና ብሔራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ ሲመለስ በአዲስ አበባ ስታዲየም በበርካታ ደጋፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል።
በፍጻሜው ጨዋታ ናይጄሪያ ቡርኪናፋሶ 1 ለ 0 በማሸነፍ የአፍሪካን ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ አንስታለች።
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2021 ካሜሮን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።
ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰችው ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጅ አገር ካሜሮን፣ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር ተደልድላ ጨዋታዋን አድርጋለች።
ኢትዮጵያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በኬፕቨርዴ 1 ለ 0 ተሸንፋለች።
በሁለተኛው ጨዋታ ዋልያዎቹ በአዘጋጇ አገር ካሜሮን 4 ለ 1 ተሸንፈዋል።
በጨዋታው ኢትዮጵያ አጥቂው ዳዋ ሁቴሳ በአራተኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ብትችልም ቪንሰንት አቡበከርና ቶኮ ኢካምቢ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የማይበገሩትን አንበሶች አሸናፊ አድርገዋል።
በወቅቱ በአሰልጣኝ ውበቱ የተመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ከቡርኪናፋሶ ጋር አንድ አቻ ተለያይታለች። ለብሔራዊ ቡድኑ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ በፍፁም ቅጣት ምት ነበር።
ኢትዮጵያ በምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት ከምድቧ የመጨረሻውን ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በቁጥሮች
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የ11 ጊዜ ተሳትፎ ኢትዮጵያ 31 ጨዋታዎችን አድርጋ 8ቱን ስታሸንፍ 19 ጊዜ ተሸንፋለች። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥታለች።
በነዚህ 31 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 33 ግቦችን ስታስቆጥር 67 ጎሎችን አስተናግዳለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ በሰፊ ግብ ያሸንችባቸው ጨዋታዎች ሁለት ናቸው። እ.አ.አ በ1962 ራሷ አዘጋጅታ ራሷ በወሰደችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቱኒዚያና ግብጽን በተመሳሳይ 4 ለ 2 አሸንፋለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫው በሰፊ የግብ ልዩነት የተሸነፈችው እ.አ.አ በ1970 ሱዳን ባዘጋጀችው ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን በወቅቱ በኮትዲቭዋር 6 ለ 1 በሆነ ውጤት ተረታለች።
ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳትፎዋ ከፍተኛ ግብ ያስተናገደችበት ሲሆን 12 ጎሎች ተቆጥረውባታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ከፍተኛ ግቦችን ያስቆጠረችባቸው ውድድሮች እ.አ.አ በ1952 እና በ1968 በቅደም ተከተል ሶስተኛውንና ስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ባዘጋጅበት ወቅት ነው። በነዚህ ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን አስቆጥራለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ አዘጋጅታለች።
ኢትዮጵያውያኖቹ አጥቂዎች ሉቺያኖ ቫሳሎና መንግስቱ ወርቁ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተመሳሳይ 8 ግቦችን በማስቆጠር በአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜም የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ዝርዝር ውስጥ 21ኛ እና 22ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
እንደ መውጫ
ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ አትሳተፍም።
የአፍሪካ እግር ኳስ መስራችና ፈር ቀዳጅ እየተባለች የምትጠራው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዎቿ ከሰሜን፣ደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ብርቱ ፉክክር በማድረግ መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ያላት ተሳትፎ እየተቀዛቀዘ መጥቶ ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ እየተሳነው ነው።
የስፖርት ቤተሰቡና ተንታኞች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት አለመቻሉ፣የእግር ኳስ እድገቱ ወደ ኋላ መቅረቱ፣ የአጥቂ መስመሩ ክፍል የአጨራረስ ድክመት፣ ለወጣት ተጫዋቾች እድል አለመስጠት፣የአሰልጣኞች በየጊዜው መለዋወጥ፣ለእገር ኳሱ የሚሰጠው ትኩረት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑና እግር ኳሱ በስፖርቱ ባለፉ ሰዎች አለመመራቱን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ይቀመጣሉ።
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2025 በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ከወዲሁ የቤት ስራዋን መጀመር ይኖርባታል። ጠንካራና ተወዳዳሪ ቡድን የመገንባት ስራ ትኩረት ያሻዋል።
ኢትዮጵያ በሞሮኮ በሚካሄደው ቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ ትሳትፍ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ቀጣይ ጊዜያት ምላሽ ይኖራቸዋል።