የአንድሬ ስቴኒን ዓለም አቀፍ ፕሬስ ፎቶ ውድድር ስራዎች ለህዝብ የሚታዩበት ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2016 (ኢዜአ)፦የዓለም አቀፍ ወጣት ፎቶ አንሺዎችን ስራዎች የሚያሳትፈው የአንድሬ ስቴኒን ዓለም አቀፍ ፕሬስ ፎቶ ውድድር ስራዎች ለህዝብ የሚታዩበት ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ።

የአንድሬ ስቴኒን ፕሬስ ፎቶ ውድድር 'ራሽያ ሲጎኒያ' ወይም የ'ራሺያ ቱደይ' የሚሰኘው የሩስያ የሚዲያ ተቋም አዘጋጅነት በመላው ዓለም የሚገኙ ወጣት ፎቶ አንሺዎች የሚሳተፉበት ፕሮጀክት ነው።


 

ከተጀመረ 10ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው እና ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 33 የሆኑ ወጣቶች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ዘንድሮም ለ10ኛ ጊዜ የተወዳዳሪዎችን ምዝገባ በይፋ ጀምሯል።

የሩስያ ሲጎኒያ የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ክሪስቲና ሊያክ እንዳሉት ውድድሩ በተለያዩ አጋጣሚዎችና በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ፎቶግራፍ ስራዎችን በበይነ መረብ ተቀብሎ በማወዳደር  ባለተሰጥኦ የዓለማችን ወጣት ፎቶ አንሺዎችን የሚያበረታታ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስካሁን ውድድሮች በአሸናፊነት የተመረጡ ከ50 በላይ ፎቶግራፎች በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ለህዝብ ዕይታ ይቀርባሉ።

የአንድሬ ስቴኒን ፕሬስ ፎቶ ግራፍ ዐውደ ርዕይ በሩስያ ባህልና ሳይንስ ማዕከል ከቀናት በፊት በይፋ የተከፈተ ሲሆን ከፊታችን ቅዳሜ ጥር 18 እስከ የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይጎበኛል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ፣ በአርጀንቲና እንዲሁም በሰርቢያ ዋና ከተሞች የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዩ ተከፍቷል።

ከትናንት በስቲያ የፎቶ ዐውደ ርዕይ መክፈቻ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን እንደተናገሩት ፤ዐውድ ርዕዩ የዘመኑን ፎቶግራፍ ጥበብ ለመመልከት ብሎም ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች በቀጣይ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ ተነሳሽነት እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።


 

በዐውደ ርዕዩ ሩስያን ጨምሮ የ16 ሀገራት ወጣት የፎቶ ጋዜጠኞች በውድድር ያሸነፉ ስራዎች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን ከ3 ቀናት በኋላ ያለ መግቢያ ክፍያ ለህዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናል።

በአዲስ አበባ የሩስያ ባሕልና ሳይንስ ማዕከል ኃላፊ አሌክሳንደር ኢቭስቲንየር፤ በታዋቂው ሩስያዊ ፎቶ ጋዜጠኛ አንድሬ ስቴኒን ስም በየዓመቱ የሚደረገው የፎቶ ውድድር ሰላም፣ ጦርነት፣ ስነ ህዝብ፣ መልክዓ ምደር፣ ስፖርት እና በሌሎች ጉዳዮች ያለ አድሎ እና በፍፁም ታማኝነት ዕውነት በምስል የሚነገርበት ውድድር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የአንድሬ ስቴኒን ፎቶግራፍ ውድድር አምስት የውድድር ፈርጆች ያሉት ሲሆን ለአሸናፊዎች ትልቁ ሽልማት 700 ሺህ የሩስያ ሩብልን ጨምሮ እንደየደረጃቸው ከ75 እስከ 125 ሺህ ሩብል ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በዘንድሮው የፕሬስ ፎቶ ውድድር መሳተፍ ለሚሹ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችም ከታች ያለውን ሊንክ በመጠቀም መሳተፍ ይችላሉ።

https://stenincontest.com/register/#register

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም