በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን መሰጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን መሰጠት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን መሰጠት መጀመሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአፋር ክልል ከጁቡቲ ድንበር በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የሚገኙ የድንበር አካባቢ ነዋሪዎችን በጠረፍ ንግድ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት ተጀምሯል፡፡
በጠረፍ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ እና የጉምሩክ የአሰራር ስርዓት ዙሪያ ለጠረፍ ነገዴዎች እና ባለድርሻ አካላት ከሰኔ 20-21 ቀን 2016 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።
ከስልጠናው ጎን ለጎንም በንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ እና ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን መመሪያ ቁጥር 935/2015 መሰረት መስፈርቱን ለሚያሟሉ ነጋዴዎች የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን እየተሰጠ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን የተሰጣቸው በአፋር ክልል ከጂቡቲ ድንበር በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ከሚገኙ የድንበር አካባቢዎች ማለትም ከኤልዳአር፣ አፋምቦ፣ አሳይታ እና ገረኔ ወረዳዎች የጠረፍ ንግድ እንዲነግዱ በአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ የተመረጡ ነጋዴዎች መሆናቸውም ተገልጿል።
በሶማሌ ክልል ከአይሻ፣ ገብለሎ እና አዲጋላ ወረዳዎች የጠረፍ ንግድ እንዲነግዱ በማህበረሰቡ ተሳትፎ ለተለዩት ነጋዴዎችም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ በኦንላይን የሚሰጥ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።