በማኅበራዊ ሚዲያ በመረጃ ልውውጥ የሚተዋወቁ ወጣቶች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
በማኅበራዊ ሚዲያ በመረጃ ልውውጥ የሚተዋወቁ ወጣቶች ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2016(ኢዜአ)፦ በማኅበራዊ ሚዲያ በመረጃ ልውውጥ የሚተዋወቁ ወጣቶች በኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት በመገኘት ደም ለገሱ፡፡
ወጣቶቹ የቴሌግራም ግሩፕ በመፍጠር መረጃ በመለዋወጥና በመማማር የሚተዋወቁ ናቸው።
በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የመማማር ዓላማን ሰንቀው ግሩፑን የጀመሩት ሲሆን፤ ቀስ በቀስ በበጎ-ፈቃደኝነት የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት በመገኘት ደማቸውን ለወገን በመለገስ በጎነታቸውን አሳይተዋል።
በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ማርያማዊት ዮሐንስ፣ ቴዎድሮስ ስንታየሁ፣ መሳፍንት መላክ እና ነብዮ ፈለቀ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሰባስበን ከመረጃ ልውውጥ ባለፈ በጎ ዓላማዎችን ሰንቀን እየሰራን ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት በአካል በመሰባሰብ በኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ በመገኘት ለወገኖቻችን ደም ለግሰናል በዚህም ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሁናቸው ጌትነት፤ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በማዋል ረገድ የወጣቶቹ ተግባር ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ከክረምቱ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መካከል በደም ልገሳ ተግባር በስፋት ለመሳተፍ ታቅዶ እስካሁን በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉንም ተናግረዋል።